ኢህአዴግ በሚያካሂደው የፖለቲካ ስልጠና ላይ ህዝቡ ቅሬታዎችን እያሰማ ነው

ጥቅምት (ሃያ ሰባ) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በየስብሰባዎቹ የተሳተፉ ምንጮች ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት በየመድረኩ የጋዜጠኞች መታሰር፣ የሃይማኖት እኩልነትና ነጻነት አለመከበር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መባባስ፣የሙስናና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት፣ የህወሃት የበላይነት መኖር፣ የድህነት መንሰራፋትና የዋጋ ግሽበት አለመቀረፍ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ወከባና እስር መጠናከር በተደጋሚሚ የሚነሱና ኢህአዴግ በቂ ምላሽ ሊሰጥባቸው ያልቻለባቸው አበይት ጉዳዮች መሆናቸው ታውቆአል፡፡

ጥያቄዎቹ በተለይ በግንባሩ አባላትና በካድሬዎች ጭምር የሚነሱ መሆናቸው ግንባሩን ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደጣለው የጠቀሱት ምንጮቻችን የበላይ አመራሩ በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን የወሰደው አቋም የለም፡፡

በተለይ ሰሞኑን በዋቢሸበሌ ሆቴል እና በፌዴራል ፖሊስ እየተካሄደ ባለው የመንግስት መገናኛ ብዙሃንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ የመንግስት ጋዜጠኞች እያነሱት ያሉት ጥያቄዎች ትምህርት ለመስጠት ከተመደቡ የኢህአዴግ ሰዎች አቅም በላይ መሆኑ ትዝብት ላይ ከመጣሉም በላይ ጠንካራ ጥያቄዎቹ እንዳስደነገጣቸው ታውቋል፡፡

በተለይ የፕሬስ ነጻነትና የጋዜጠኞች የጅምላ  እስርና ስደት ጉዳይ የተነሱ ጥያቄዎች ተድበስብሰው መታለፋቸው በርካታ ጋዜጠኞችን አሳዝኖአል፡፡ አንዳንዶቹም መግባባትና መተማመን ለማይገኝበት ስብሰባ ለምን የህዝብ ሐብትና ገንዘብ እንደሚባክን በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡