ኀዳር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝና ከቢኔያቸው በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ተወካይ ከተባሉ ሰዎች ጋር በተደረገው ውይይት ኢህአዴግ የኔ በሚላቸው አባሎችና ደጋፊዎች ከፍተኛ ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡
ወ/ሮ አስቴር ማሞ የሚመሩት የህዝብ አገልግሎትና የሰው ኃይል ልማት ሚ/ር አዘጋጅቶት ባለፈው ዕረቡ በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት በተካሄደው ውይይት ላይ በተለይ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የሚባሉት እንደፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ፍ/ቤቶች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የሚሰሩ ተቋማት ሆነው ሳለ ፣ በአሁኑ ጊዜ በተጨባጭ ከዚህ በተቃራኒ ህዝብን የሚያስለቅሱ የሌብነት ማእከላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ከወንጀለኞች ጋር አብሮ የሚታይ መሆኑ፣ ንጹሃን ሰዎችን አለአግባብ ማሰር፣ ማንገላታት እንዲሁም መክሰስ፣መደብደብ፣ የፍትህ ስራ ለማከናወን ጉቦ በፊት ለፊት መጠይቅ፣ ወንጀለኞች እንዳይከሰሱ በእርቅ ሰበብ ከሳሽ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ፣ ፍርድን ማዘግየትና በመሳሰሉ ችግሮች ሕዝብ እየተበደለ መሆኑ መነገሩን ስብሰባውን የተከታተሉ ወገኖች ጠቁመዋል፡፡
በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍም ፍትሐዊ ስርዓት ያለመኖር ፣ የሚወጡ መመሪያዎች ለሁሉም በእኩል ተግባራዊ ያለማድረግ፣ የተወሰኑ ነጋዴዎችን ለመጥቀም አሻጥር መስራትና በግብርና ቀረጥ ሰበብ ሰዎችን ማጥቃት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡ በስብሰባው ላይ በጥንቃቄ የተለዩና በተለያየ አደረጃጀቶች የተጋበዙ ሰዎች የተገኙ ቢሆንም ባልተጠበቀ መልኩ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በተለይ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ አደጋ ውስጥ መሆኑ በግልጽ ቋንቋ መናገራቸው ብዙዎችን አመራሮች አደናግጦአል፡፡
አንዳንድ የኢህአዴግ አመራሮች ይህ ችግር ራሱ ኢህአዴግ የለያቸውና እታገላለሁ ብሎ ቃል የገባቸው ችግሮች ናቸው ብለው በመድረኩ ላይ ለማቃለል ቢሞክሩም፣ በመድረኩ የተነገሩት ስር የሰደዱ ችግሮችና የሰዎቹ ጠንካራ አቁዋም ያልተጠበቀ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የአዲስአበባ ማዘጋጃ ቤት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውሃ መ/ቤቶች እንዲሁ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸው ተነግሮአል፡፡