በረሀቡ ምክንያት ዜጎች መሰደድ ጀምሩ

ኀዳር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ጎንደር እብናት ወረዳ በሚገኙ 11 ቀበሌዎች አርሶአደሮች በቂ የሆነ እርዳታ ሊቀርብላቸው ባለመቻሉ በርካታ ሰዎች ቀያቸውን እየጣሉ በሌሊት መሰደዳቸው ታውቋል። እስካሁን ያልተሰደዱትም ቢሆኑ፣ በታጣቂዎች እየተጠበቁ መሆኑን ጉዳዩን ለማየት ወደ አካባቢው የሄዱ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህም ላይ ተረጅዎች የመሬት ግብር ክፈሉ ተብለው ሲገደዱ፣ “የት አምጥተን እንከፍላለን” ብለው መጠየቃቸውንና፣ የመንግሰት ካድሬዎች ” እርዳታ ታገኛላችሁ፣ እርዳታውን ሽጣችሁ ክፈሉ” የሚል መልስ ሰጥተዋቸዋል። በርካታ ሰዎች ግብር ለመክፈል አንችልም በማለታቸው ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውንም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ባለሙያው ተናግረዋል። በዚሁ አካባቢ 10 ከብቶቹን ያጡ አንድ ሰው ራሳቸውን ሰቅለው ገድለዋል። በርካታ ህጻናትም ወላጆቻቸው ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት ሲሄዱ፣ቤት ጠባቂ በመሆናቸው ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ባለሙያው ገልጸዋል።
መንግሰት ረሃቡን ለመደበቅ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ባለሙያው ገልጸዋል። የመገናኛ ብዙሃን ረሃቡን ተከታትለው ይፋ ካላደረጉት ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ድጋፍ ድርጅት የትምህርት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ድርቁ በሚታይባቸው ዋና ዋና ወረዳዎች እስካሁን 2 ሚሊዮን ህጻናት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ከእነዚህም መካከል 47 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ። ወላጆች ምግብና ውሃ ፍለጋ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሰደዳቸው ልጆች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣በሁለት ተጨማሪ ወረዳዎችም በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።