በኦሮምያ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው

ኀዳር ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተከትሎ ተማሪዎች የሚያሰሙት ተቃውሞ ዛሬ በቦረና ዞን በቡሌሆራ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ተነስቶ ታምሩ አኖሌ የተባለ መምህር ጉዳት ደርሶበታል። በተማሪዎች ላይ በተወሰደው እርምጃም የተወሰኑ ተማሪዎች ሳይጎዱ እንዳልቀረ የአካባቢው ምንጮች ግልጸዋል።
ተቃውሞው በነቀምቴ፣ ወሊሶ፣ በምስራቅ ሃረርጌ አወዳይና በምእራብ ወለጋ ግዳሚ ከተማ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተካሄደ ሲሆን፣ በተቃውሞው የሞቱ ተማሪዎች ባይኖሩም በድብደባ የቆሰሉ ተማሪዎች አሉ።
ተቃውሞው ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ከ4 ያላነሱ ተማሪዎች በጸጥታ ሃይሎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል። መንግስት ተመሳሳይ ተቃውሞ የሚቀጥል ከሆነ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል። መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ከአገር ውስጥ መድረክ ከውጭ ደግሞ አርበኞች ግንቦት7 አውግዘውታል።