አፍሪካ ሚስጢራዊ በሆነ ስምምነት ሀብቷን እየተዘረፈች ነው ተባለ

ግንቦት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቀድሞውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ  ኮፊ አናን ፣ የቀድሞውን የናይጀሪያ መሪ ኦለሱጎን ኦባሳንጆ እንዲሁም የኔልሰን ማንዴላን ባለቤት ግራሻ ሚሸልን ያቀፍ የጥናት ቡድን ይፋ ባደረገው ጥናት አፍሪካ ግልጽነት በጎደለው ሚስጢራዊ ድርድሮች የተፈጥሮ ሀብቷን እየተዘረፈች ነው።

ከታክስ ማጭበርበር ፣ በድብቅ በሚካሄድ የማእድን ማውጣት እና በህገወጥ መንገድ ገንዘብ ወደ ውጭ ከመላክ ጋር በተያያዘ አፍሪካ በየአመቱ 38 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ ተመልክቷል።

አፍሪካ በእያመቱ በእርዳታ የምታገኘውን ሁለት እጥፍ ገንዘብ በህገወጥ መንገድ እንደምታጣ ኮፊ አናን ገልጸዋል። በአጉሪቱ ግልጽነት እንዲሰፍን የአፍሪካ መሪዎች በተጠያቂነት ዙሪያ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ኮፊ አናን ጠይቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የተባለው ተቋም ባወጣው ጥናት በኢትዮጵያ ባለፉት 9 አመታት ከ11 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ150 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተዘርፎ ወደ ውጭ መውጣቱን መዘገቡ ይታወሳል።