ታዋቂ የኢትዮጵያ ሶማሊ ተወላጆች የክልሉ ፕሬዚዳንት በድብቅ ያደረጉት ንግግር እየነቀፉ ነው

ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ወቅት ለሶስት አመታት በዲፕሎማትነት፣ በመምህርነት እና በጋዜጠኝነት የሰሩትና በርካታ የታሪክ መጽሀፎችን የጻፉት አቶ መሀመድ ሀሰን ለኢሳት እንደተናገሩት ፣ የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሀመድ ኡመር  የተናገረው ከወያኔ በስሎ የቀረበለትን ነው በማለት ተናግረዋል። “ግለሰቡ ያልተማረ ነፍሰ ገዳይ ነው” የሚሉት አቶ ሙሀመድ ፣ የመለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ እንደነበረም ገልጸዋል። ክልሉ ለወያኔ ጄኔራሎች የመወፈሪያ ክልል ነው ያሉት አቶ ሙሀመድ፣ ፕሬዚዳንቱ የተናገሩትም የራሳቸውን ባለመሆኑ እንደ ቁም ነገር አይቆጠርም

ኢሳት ይፋ ያደረገው ቪዲዮ የክልሉ ባለስልጣናት የአመራር ብስለት ምን ያክል ደረጃ እንደደረሰ  ያሳያል ያሉት አቶ ሀሰን፣ የአመራር ችሎታ ያላቸው ሰዎች እንደማይፈለጉ ገልጸዋል

የፌደራሉ መንግስት በፕሬዚዳንቱ ላይ እርምጃ የሚወስድ ይመስልዎታል? ተብለው የተጠየቁት አቶ አብዲ ፣ ኢህአዴግ እሱን የመሰለ ጨካኝ ሰው እንደማያገኝ ገልጸው፣ ዋናው ነገር ኢህአዴግ መልእክቱን በግለሰቡ በኩል በማስተላለፉ አጠቃላይ የመንግስትን ፖሊሲ ለማወቅ መርዳቱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ( ኦብነግ) የውጭ ግንኙነት ሐላፊና ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሀሰን አብዱላሂ በበኩላቸው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት በትክክልም የወያኔን ፖሊሲ ነው ብለዋል

እኛ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ጥላቻ የለንም ያሉት አቶ ሀሰን፣ ወያኔ ህዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት የሚጠቀምበት ስልት ነው ብለዋል።

መንግስት በፕሬዚዳንቱ ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለው ያስባሉ ተብለው የተጠየቁት አቶ ሀሰን “በፍጹም” በማለት መልሰዋል

ኢሳት የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሀመድ በድብቅ ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።