ህዳር 11 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኤምባሲዎቹ ምሬታቸውን የገለጹት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ዋነኛ ከሚላቸው የኮርፖሬት ደንበኞቹ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ በሒልተን ሆቴል ባካሄደው የሐሳብ ልውውጥ መድረክ ነው።
ከኤምባሲዎቹ በተጨማሪ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ጭምር ምሬታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ቴሌን ካማረሩት አስተዳደራዊ መስሪያ ቤቶች መካከል የአዲስ አበባ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ይገኝበታል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ በስልክና በ ኢንተርኔት አገልግሎት ፤ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ሳይቀር የማትሻልና ከአፍሪካ አህጉር መጨረሻ ላይ የምትገኝ ናት።
በተለየ መልኩ ኤምባሲዎች፣ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ና ሌሎች የቴሌ ደንበኞች በተገኙበት
በዚሁ የሀሳብ ልውውጥ ስብሰባ፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ፈፅሞ ያልጠበቀው ምሬትና ቅሬታ መሰንዘሩ ተሰምቷል።
በተለይ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች በድርጅቱ አሠራር ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳላቸው ከመናገራቸውም ባሻገር በአገልግሎቱ ተስፋ እስከመቁረጥ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት መማረራቸውንና ተስፋ መቁረጣቸውን ካስታወቁት መካከል፣ የብራዚል ኤምባሲ ተወካይና የድርጅታቸው ስም እንዳይጠቀስ የፈለጉ የሐዋላ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሳይቀር በቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያለውን ቅሬታ በተወካዩ በኩል በመድረኩ ላይ ማስተላለፉ ታውቋል፡፡
ድርጅቱ ወደ ኢትዮ-ቴሌኮም መዛወሩን ተከትሎ በመላ አገሪቱ በቴሌ ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ብዙ ሽህ ሰራተኞች ከሥራ መሰናበታቸው ይታወሳል።
የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን ለማሻሻል በሚል ድርጅቱ ለኢትዮ ቴሌኮም እንዲሰጥ ቢደረግም፤ ከመንግስታዊ ቁጥጥር ተፅዕኖ ባለመላቀቁ አገልግሎቱ እየከፋ እንጂ እየተሻሻለ ሊመጣ እንዳልቻለ
ምንጮች ይናገራሉ።
በተለይ የ ዓረቡን ዓለም አብዮት ተከትሎ ወትሮም ከ ዜሮ ነጥብ 5 በመቶ የማይበልጠው የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ሽፋን ይበልጥ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ይደመጣሉ።
እንዲሁም ድርጅቱ ወደ ኢትዮ-ቴሌኮም መዛወሩን ተከትሎ ማኔጅመንቱ በሙሉ በቅርቡ በጡረታ መልክ ከሰራዊቱ እንዲገለሉ በተደረጉ የህወሀት ጀኔራሎች ስር እንዲወድቅ መደረጉ፤ በኢንተርኔትና በስልክ መስመሮች ላይ አልፎ አልፎ ይስተዋል የነበረውን መቆራረጥ እና የሳይበር ጠለፋውን እንዳባባሰው ይነገራል።
በቅርቡ ፦”ፍትህና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር መኖር አልፈልግም” መምህር የኔሰው ገብሬ ራሱን በ እሳት ማቃጠሉ እንደተሰማ፤ ወደ አካባቢው የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች በ አስቸኳይ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ መደረጋቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የስልክ ጠለፋ እንደሚያካሂድ በቅርቡ በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት በቀረቡት በእነ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና መምህርትና ጸሀፊ ርእዮት አለሙ ላይ
ማስረጃ ባቀረቡበት ወቅት ስልኮችን እንደሚጠልፍ በራሱ ላይ አረጋግጦል::