በመላው አለም የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን፣ መምህር የኔሰው ገብሬን ፎቶግራፍ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል

ህዳር 11 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመላው አለም የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን፣ በቅርቡ የመንግስትን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በመቃወም እራሱን አቃጥሎ የተሰዋውን መምህር የኔሰው ገብሬን ፎቶግራፍ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።

ሁኔታውን በቅርበት የተከታተሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን እንደገለጹት ከሆነ፣ ፌስ ቡክ በመባል የሚታወቀው የኢንተርኔት መገናኛ መድረክ በአለም ዙሪያ ከ8 መቶ ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ሲኖሩት በቅርቡም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር አንድ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያውያኑ የራሳቸውን ፎቶግራፎች ገለል አድርገው የኔሰው ገብሬን ፎቶግራፍ የሚጠቀሙበትን ምክንያት ሲያስረዱም “ወንድማችን የኔሰው በሀገራችን ውስጥ ነጻነት፣ ዲሞክራሲ እና የህግ የበላይነት እንዲመጣ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት በመነሳት እራሱን በ እሳት አቃጥሎ መሰዋቱን በቀላል እንደማንመለከተው እና እሱ የተሰዋለትን አላማ አንግበን እንደምንታገል ለመግለጽ ነው” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ የየኔሰው ገብሬን ፎቶግራፍ ለምን እንደሚጠቀሙ ሲያስረዱ “ጉዳዩ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ”መሆኑን ገልጸዋል።

በቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና የሌሎችም ሀገራት ለውጥ አራማጆች በንቅናቄያቸው ወቅት የፌስ ቡክን የመገናኛ መረብ በመጠቀም ህዝቡን ለማስተባበር፣ ለማነሳሳት እና ንቅናቄያቸውን ለማቀናጀት እንደተጠቀሙበት ይታወቃል።

የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት በኢትዮጵያ እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ የለውጥ አራማጆች እንደ ሌሎቹ የአረብና የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ኢንተርኔትን እና እንደ ፌስ ቡክ ያሉ የመገናኛ መረቦችን በአግባቡ ሊጠቀሙ ባይችሉም እንኳ፣ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለውጥ አራማጆች በከፍተኛ ሁኔታ የፌስ ቡክ፣ የትዊተር፣ የዩትዩብ እና ፓልቶክ የመገናኛ መረቦችን በስፋት ይጠቀማሉ።

በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራቶች ዉስጥ በኢትዮጵያ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል። ከፌስ ቡክ ኦፊሽያል ድረ-ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ 401 ሺ160 የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንተርኔትን ከሚጠቀመው ማህበረሰብ 90% የፌስ ቡክም ተጠቃሚ መሆኑን የቫንኮቨሩ ዳግም ዘገባ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዬኔሰው ገብሬ አድናቂዎች የሀዘን መግለጫዎችንና የተነሱ ጥሪዎችን  እያስተላለፉ ነው።

የቶሮንቶ የሰብአዊ መብቶችና የዲሞክራሲ ህብረት በየኔሰው ገብሬ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጦ፣ የካናዳ መንግስት ለመለስ ዜናዊ መንግስት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቋርጥ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ አባል የሆነው ዮናታን ወግደረስ በበኩሉ የየኔሰው ሞት ለሁለት ቀን ያክል ህመም ፈጥሮበት እንደነበር ገልጦ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግፍ አገዛዝ እንዲያበቃ ሁላችንም
በጋራ እንነሳ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ግንቦት7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ባወጣው መግለጫ በመምህር የኔሰው ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጧል።

ንቅናቄው የመምህር የኔሰው ሞት ያለውን ታሪካዊና ወቅታዊ ፋይዳ ሲገልጥ “መምህር የኔሰው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ አስከፊነት መገለጫ ሆኗል። መምህር የኔሰው በህይወት እያለም፤ እየሞተም፤ ከሞተም በኋላ መምህር ሆኖ አስተምሮናል። መምህር የኔሰው፣ “እየኖርን ነን” እያልን እራሳችን እያታለልን ላለነው ሁሉ ላይ ከፍ ያለ የሞራል እዳ ጥሎብን አልፏል።” ብሎአል።

“የመምህር የኔሰው መልዕክት ግልጽ ነው” የሚለው ግንቦት7 ” ፍትህና ነፃነት በሌሉበት፤ መብት በረገጠበት ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም። የባርነት ኑሮ፤ ኑሮ አይደለም። እውነቱን ለመናገር ባለፉት ሃያ ዓመታት ኢትዮጵያዊያን እየኖርን ያለነው “ኑሮ” ኑሮ አይደለም። ዓይኖቻችን እያዩ፤ ጆሮዎቻችን እየሰሙ አንድ ጠባብ፣ ዘረኛና ትዕቢተኛ የሆነ ትንሽ ቡድን መላዋን ኢትዮጵያ ጠፍንጎ አስሮ እያለባትም፤ እያዋረዳትም ነው። አገራችን በአንድ ቡድን ስትመዘበር መከላከል አቅቶን በድናችንን እየኖርን ነው። ባርነት ይለመዳል። እኛም ለሃያ ዓመታት ባርነትን ተለማምደናል። መምህር የኔሰው የለኮሳት እሳት ካላነቃችን መቼም ላንነቃ እንችላለን።”
ሲል ገልጧል።

ታዋቂው የህግ ባለሙያና ጸሀፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አለማዬሁ ገብረማርያም “ነጻነቴን ስጡኝ ወይም ግደሉኝ” በሚል ርእስ ባወጡት ጽሁፍ የኔሰው ፣ በአለም ላይ ለነጻነታቸው ሲሉ ራሳቸውን ከሰውትና ለዘላለሙ
በታሪክ ሲዘከሩ ከሚኖሩ ጀግኖች መካከል ተቀላቅሎአል” ብለዋል።