አዲስ አበባ መስተዳድር ከንቲባ በአማካሪዎች ብዛት ተጨናንቀዋል

ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት የመስተዳድሩም ምንጮች እንደገለጹት የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በአማካሪዎቻቸው ብዛት ተጨናንቀዋል። አማካሪዎቹ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሹሙ የሚመጡ በመሆኑ፣ ከንቲባው ግራ ተጋብተዋል። አማካሪ የሚባሉት ሰዎች በጸሃፊያቸው በኩል አስፈቅደው ወደ እርሳቸው ቢሮ ከገቡ በሁዋላ ” እኔ እኮ የዚህ ዘርፍ አማካሪዎ ነኝ” ሲሉዋቸው፣ ከንቲባው በመደናገጥ ” ከስራ ብዛት ነው ያላወኩዎት” በማለት ይቅርታ እየጠየቁ ማሰናበት የተለመደ ተግባር ሆኗል።
ከንቲባው 10 በምክትል ከንቲባ ማእረግ የሾሙዋቸው የዘርፍ አማካሪዎች አሉዋቸው። ይሁን እንጅ በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ የዘርፍ አደረጃጃቶች በመኖራቸው እርሳቸው ፈርመው የሾሙዋቸውም ይሁን ከድርጅቱ የሚሾሙትን አማካሪዎችን ለይተው ለማወቅ ባለመቻላቸው፣ አማካሪዎቹ፣ ራሳቸውን እንዳማካሪ እየጠቀሱ በስብሰባዎች ላይ ሁሉ አስተያየት ሲሰጡ ከንቲባው በከፍተኛ ሁኔታ ይደናገጣሉ። በተለይም እርሳቸው የማያዉቋቸው ሰዎች ስራቸውን በተመለከተ በግምገማ ወቅት አስተያየት ሲሰጡ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የሚገቡት አቶ ድሪባ፣ ድንጋጤያቸው ለመደበቅ አለማወቃቸውን እንደምክንያት እንደሚያቀረቡ የውስጥ ታዛቢዎች ገልጸዋል።
አቶ ድሪባ የኦህዴድ አባል ቢሆኑም፣ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎች የሚተላለፉት በህወሃቶች ነው። ይሁን እንጅ ኢህአዴግ ስራ ያጡ አባሎቹን ለመያዝ ሲል በየጊዜው የሚሰጠው ሹሙት የአገር ሃብትን ከማባከን የዘለለ ውጤት እንደሌለው ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው በቅርቡ በተደረገው ግምገማ ዝቅተኛ ነጥብ በማምጣታቸው ባሉበት ቦታ ላይ ላይቀጥሉ ይችላሉ ተብሏል።