ፍርድ ቤቱ በነፃ ያሰናበታቸውን እስረኞች ከእስር ቤት አልወጡም

ነኅሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብርተኝነት ወንጀል ከተጠረጠሩ በኋላ፤ በእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ፣ ከአንድ ዓመት በላይ ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ሲታይ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት በነጻ እንዲሰናበቱ ከተፈረደላቸው አምስት ግለሰቦች መካከል 2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው እና 7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን እስከአሁን ድረስ ከቂሊንጦ እስር ቤት መፈታት ባለመቻላቸው የተነሳ፣ በዛሬው ዕለት ማረሚያ ቤቱ ላይ ክስ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
እስረኞቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የመፍቻ ትዕዛዙ ለማረሚያ ቤቱ ቢደርስም፣ ተከሳሾቹ እስከአሁን ድረስ ከእስር ሊለቀቁ አልቻሉም።
‹‹የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እና ተከሳሾቹ እንዲለቀቁ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው የ2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው ባለቤቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አዛናው እና የ7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሠለሞን ወላጅ እናት ወ/ሮ መሠረት ገ/ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት ትዕዛዙን ለሰጠው ችሎት ክሳቸውን ማቅረባቸው ታውቋል ሲል ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በፌስቡክ ገፁ ዘግቧል።