አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በአፋጣኝ የሕዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝባዊ መንግስት እንዲያቋቁሙ ሲሉ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባርና የጎንደር ኅብረት ጠየቁ

አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በአፋጣኝ የሕዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ሕዝባዊ መንግስት እንዲያቋቁሙ ሲሉ ሰማያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባርና የጎንደር ኅብረት ጠየቁ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ/ም) “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመላው ኢትዮጵያ እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነትን ተከትሎ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። አገዛዙ ለሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሳይሰጥ በተደጋጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት የዜጐችን ደም ማፍሰስ፣ በጅምላ ማሰር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጣሱን ተያይዞታል፡፡ ይሁንና ሕዝባዊ ትግሉን የመንግስት አፈና ከቶውንም አላስቆመውም” ሲል ሰማያዊ ፓርቲ መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዙ ካደረሰበት እጅግ የከፋ ስቃይ አንፃር አሁን የሚነሳው ጥያቄ ሥርዓቱን የመጠገን ሳይሆን ስርዓቱን የመለወጥ ስለሆነ፣ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋምና ከአፋኝ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲሆን ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ያለው ፓርቲው፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በፓርላማ ያሰሙትን ንግግር አወንታዊ ቢሆንም፣ መሬት ወርዶ በተግባር መተርጎሙ ላይ ጥርጣሬ እንዳለውም ጠቅሷል።
የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከህዝባዊ እምቢተኝነቱ መጠንከር የተነሳ ህገመንግስትን እስከማሻሻል ለማድረስ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ቢገልፁም፣ ችግሩ በጊዜው ረገብ እንዳለ የገቡትን ቃል ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውን ያስታወሰው ፓርቲው፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የገቡትን ቃል በተለይም አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና “በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል” የሚሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሲቪክ ማህበራትን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቀራረብ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የሆነው ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው ብሎአል።
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት በገቡት ቃል መሠረትም ቃላቸውን ይተገብሩ ዘንድ፣ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት ከወዲሁ ጥሪጊያ መንገዱን ሊያመቻቹ ይገባል ያለው ፓርቲው፣ ሥራቸውን በይፋ በጀመሩ ቀናት ይህንን አፋኝ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሱ ጥሪ አቅርቧል።
በመንግስት ቸልተኝነት እና የአስተዳዳር በደል ምክንያት ብቻ በተፈጠረው አለመግባባት ከመላ አገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሰው እንዲቋቋሙ፤ ዜጎቻችንን ለዚህ ችግር የዳረጉ የመንግስት ሹመኞች በበደሉት መጠን ፍትህ እንዲዳኙ፣ የፍትህ ተቋማትንና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ ለመድበለ ፓርቲ መጠንከር እና ለዴሞክራሲና ለፍትሕ እድገት ዋንኛ ማነቆ የሆኑት ተቋማት በአዲስ መልክ ተዋቅረው በነፃነት ህዝብን እንዲያገለግሉ ፓርቲው ጠይቋል።
የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር ፓርቲ በበኩሉ የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር መመረጥ የኢህአዴግ የተለመደ ድራማ ወይስ የለወጥ ፈላጊ ድርጅቶች ጥረት? በሚል ር ዕስ ባወጣው መግለጫው፣ ሹመቱ፣በህውሃት የበላይነት ስትመራ የቆየችውን ኢትዮጵያን ሰላም የሰፈነባት ፍትህ የተረጋገጠባትና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠባት አገር ለማየት ታጋዮች ባደረጉት ቁርጠኝነት የተከናወነ ከሆነ እሰየው እንላለን።
የለውጥ ፈላጊ ትውልድን ትግል ለመግታት እና የእፎይታ ጊዜ ለመውሰድ ታስቦ ከሆነ ግን የለውጥ ፈላጊውን ትውልድ ትግል ማንም ሊገታው አይችልም ያለው ግንባሩ፣ ትግሉ የተቀጣጠለ ሰደድ መሆኑን በመገንዘብ በአገሪቷ ለረጅም ዓመታት በጉጉት ይጠብቅ የነበረው እውነተኛ የፌደራል ስርዓት እውን እንዲሆን ጠይቋል።
ግንባሩ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፣ የፖሊቲካ፤ የሃይማኖትና የሰበዓዊ መብት ታጋዮችን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ግልጽና እውነተኝነት በተሞላበት መንገድ የውይይት መድረክ መክፈት፣ የፖሊቲካና የዲሞክራሲውን ምህዳር በማስፋት የመጻፍና የመሰብሰብ መብትን ማክበር፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የሴኩሪቲና የመከላከያን የበላይነት ከክልሎች በማስወገድ በነጻነት የራሳቸውን ክልል እንዲያስተዳድሩና የሕዝቦቻቸውን ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ ይገባቸዋል ብሎአል።
“በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው ቀዬያቸው ለተፈናቀሉ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጎዱ የሞያሌና አካባቢዋ ኑዋሪዎች የመልሶ ማቋቋም ስራ በአፋጣኝ እንዲሰራም ጥሪ አቅርቧል። በተጨማሪም ለአገራችንና ለሕዝባችን አዲስ ምእራፍ በመክፈት በነጻ መድርክ ውይይትና ግልጽነት የተሞላበት መግባባት በመፍጠር ውድ ኢትዮጵያችንን አብረን መገንባትና ፤ እድገትና ብልጽግናዋን ለማስፋትና ለማሳደግ እንድንችል፤ ይህን መልካም አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት እናሳስባለን ሲል መግለጫውን ቋጭቷል።
የጎንደር ኅብረት በበኩሉ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ተቻችሎ መኖር በመዘከር ያሰሙት ንግግርን አወድሶ፣ ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
መብታቸውና ማንነታቸው እንዲከበርላቸው በመጠየቃቸው ብቻ እንደ አሸባሪ ተቆጥረው ለረዥም ጊዜ በየእስር ቤቱ ታስረው፣ ጨለማ ቤት የተዘጉት የሞራል ካሳ ተሰጥቷቸው በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ድጋሚም በፖለቲካ እይታቸው ምክንያት ዜጎች ወደ እስር ቤት የማይወረወሩ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ፣ ዜጎችን እጅ ከወርች አስሮ የያዘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሱና አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ እርቅ የሚጠራበትን መድረክ ተፈጥሮ የሽሽግግር መንግሥት የሚዋቀርበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ህብረቱ ጥሪ አቅርቧል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ “ተፎካካሪ” ብለው ለጠሯቸው በተለያየ አመለካከት የተደራጁ ድርጅቶች ለደህንነታቸው ዋስትና ያለው አዋጅ በማወጅ በሰላም ወደ አገራቸው ገብተው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ራእይ የሚሸጡበትን መድረክ ያዘጋጁ ዘንድ እንጠይቃለን ያለው የጎንደር ህብረት፣ ዶ/ር አብይ ይዘው የተነሱትን ቀናኢ ርዕያቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሕዝቡ ትግሉን የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሎአል።