በባህርዳር ታስረው የነሩ 19 ሰዎች ከእስር ተለቀቁ

በባህርዳር ታስረው የነሩ 19 ሰዎች ከእስር ተለቀቁ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ/ም) ያልተፈቀደ ስብሰባ አድርጋችሁዋል በሚል ላለፉት 2 ሳምንታት በእስር ቤት ያሳለፉት የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ጋዜጠኞች፣ ጠበቆችና በተለያዩ ሙያዎች ተሰማርተው የሚገኙ 19 ሰዎች መፈታታቸው ታውቋል።
ታስረው ከተፈቱት መካከል በባህርዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚደንት የሆነው ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበረና የ”አንፀባራቂው ኮከብ” መፅሃፍ ፀኃፊ አቶ ጋሻው መርሻ፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና አሁን በጥብቅና ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኘው የሱፍ ኢብራሂም፣ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆነው ተመስገን ተሰማ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር በለጠ ሞላና የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ ይገኙበታል። ምሁራኑ ለአማራ ህዝብ አማራጭ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም አስበዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በሌላ በኩል ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 12 ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አርማ የሌለውን ሰንደቅ አላማ ተጠቅማችሁዋል በሚል ከታሰሩ በሁዋላ የመታወቂያ ዋስ የተጠየቁ ቢሆንም፣ ዜናውን እስካጠናከርበት ሰዓት ድረስ አልተለቀቁም።