ህወሃት የሶማሊ ክልል ባለስልጣናት በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ እንዲካተቱ ግፊት እያደረገ ነው

ህወሃት የሶማሊ ክልል ባለስልጣናት በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ እንዲካተቱ ግፊት እያደረገ ነው
(ኢሳት ዜና መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ/ም) ከመጀመሪያው ጀምሮ የዶ/ር አብይ አህመድን የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትና ጠ/ሚኒስትርነት ሹመት አጥብቆ ሲቃወመው የነበረው ህወሃት፣ በካቢኔው ውስጥ ተጽኖ ለመፍጠር እና በብአዴንና በኦህዴድ መካከል ተፈጥሯል የሚለውን መርህ አልባ ግንኙነት ለመበጠስ በማሰብ የኢትዮ-ሶማሊ ክልል ባለስልጣናት በቂ የስልጣን ቦታ እንዲሰጣቸው ግፊት ማድረግ ጀምሯል።
ህወሃት የኢትዮ-ሶማሊያውያን በፌደራል መንግስቱ በቂ የሆነ ቦታ የላቸውም የሚል አጀንዳ ይዞ የመጣ ሲሆን፣ አሁን ካላቸው የሚኒስትርነት ቦታዎች በተጨማሪ እስከ 4 የሚደርሱ የሚኒስቴርና የምክትል ሚኒስቴር ቦታዎች እንዲሰጡዋቸው ጥያቄ በማቅረብ ላይ ነው። ዶ/ር አብይ ይህንን ጥያቄ እንዲቀበሉ ግፊት ማድረግ የጀመረው ህወሃት፣ ጥያቄው በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ተቀባይነት ካገኘ፣ ክልሉን በበላይነት የሚመሩት አቶ አብዲ ኢሌ -በሶህዴፓ በኩል የሚሾሙ ሚኒስትሮችን ያቀርባሉ።
በሶህዴፓ በኩል የሚቀርቡት የሶማሊ ክልል ባለስልጣናት ለአቶ አብዲ ኢሌና ለህወሃት ታማኞች ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን፣ በካቢኔው ውስጥ ማንኛውንም የህወሃት አቋም እንዲደግፉ ግዴታ ይገባሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብአዴንንና ኦህዴዴን ሃሳቦች በመደገፍ የህወሃትን አጀንዳዎች ውድቅ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ስጋት የገባው ህወሃት፣ በካቢኔ ምርጫ ላይ የሶማሊ ክልል ተወካዮች በቂ ቦታ እንዲኖራቸው እየሰራ ነው።
ህወሃት በብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚወነጀሉት አቶ አብዲ ኢሌ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ አዳዲስ ግጭቶችን ለመፍጠር መዘጋጀቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ጠ/ሚኒስትሩ በተሾሙ ማግስት የሶማሊ ልዩ ሃይል ከአልሸባብ ጋር ጦርነት እንዳደረጉ ተደርጎ የቀረበውን ሪፖርት በዋቢነት ጠቅሰዋል። የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት አልሸባብ በክልሉ ውስጥ አይንቀሳቀስም። እንደ አልሸባብ ሆነው እንዲተውኑ የሚደረጉት፣ በአብዲ ኢሌ የሚታዘዙት የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ናቸው። የአልሸባብ ማንሰራራት እንደ ዜና እንዲቀርብ የተፈለገው የሶማሊ ክልል አሁንም መረጋጋት የሌለው እንደሆነ በማሳየት አብዲ ኢሌ በስልጣን ላይ እንዲቆይና ግለሰቡን በሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጅሎ ለማስነሳት የሚደረገውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማክሸፍ ነው።ይህንንም ህወሃት በወታደራዊ አዛዦቹ የነደፈው እቅድ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ። የህወሃት ወታደራዊ አዛዦች አብዲ ኢሌ የሰብአዊ መብቶችን መጨፍለቁን ቢስማሙበትም፣ ክልሉን ከአልሸባብና ከኦብነግ በመታገድ ሰላም አምጥቷል በማለት ሲያወድሱት ቆይተዋል።
ክልሉ ያልተረጋጋ እንደሆነ በማሳየት አብዲ ኢሌ በስልጣን ላይ እንዲቆይ የማድረጉ እቅድ ከተሳካ፣ ህወሃት በአልሸባብ ወይም በሌላ ታጣቂ ስም በምስራቅ በኩል በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጥቃት በመፈጸም በዶ/ር አብይ አስተዳደር ላይ ተጨማሪ ጫና ሊፈጥር ይችላል። በአሁኑ ሰዓት የአልሸባብን ሚና ወስደው የሚተውኑት የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በሶማሊና ኦሮምያ ድንበሮች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ ሲሉ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
አቶ አብዲ ኢሌ በዶ/ር አብይ የእራት ግብዣ ላይ የተገኙ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስልክ በማውራት እንዳጠፉ ስነስርዓቱን የተከታተሉት ሰዎች ገልጸዋል። ዶ/ር አብይም ሆኑ ሌሎች የኦህዴድ ባለስልጣናት ጠ/ሚኒስትር ሆነው እንዳይሾሙ አብዲ ኢሌ ከህወሃት ጋር በመሆን ከፍተኛ ዘመቻ ሲያካሂድ ቆይቷል። በአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ንግግር ደስታቸውን የገለጹት የክልሉ ነዋሪዎች ቤተሰቦች ፣ማስፈራሪያ የደረሳቸው መሆኑንም ምንጮች አክለው ተናግረዋል።
የህወሃት አባላት ከእንግዲህ ጠ/ሚኒስትሩን ፊት ለፊት እንዳይቃወሙ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ታውቋል። የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች አባሎቻቸው እንዲረጋጉና በሂደት እንዲፈርዷቸው የማሳመን ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውንም የኢሳት ምንጮች አክለው ገልጸዋል።