አንድነት ፓርቲ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄደ

ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ሚያዚያ 26 ባካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በስርአቱ ላይ ያላቸውን ምሬት ገልጸዋል።

በሰልፉ ላይ በአዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄደው የውሃ እጥረት፣ የመብራት እና የስልክ ኔት ወርክ እጥረት እንዲቀረፍ ጥሪ ቀርቧል።

በቅርቡ በኦሮምያ በንጹሃን ተማሪዎች ላይ የመንግስት ታጣቂዎች  ያደረሱትን ግድያ፣ ሀሳባቸውን በሚገልጹ ጋዜጠኞችና ጸሃፊዎች ላይ የደረሰውን እስርም ሰልፈኛው አውግዟል።

የተሳሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን እንዲያሰፋ የሚጠይቁ መልእክቶችም ተላልፈዋል።

ሰልፈኞቹ ከያዙዋቸው መፈክሮች መካከል ” ስራና ሰራተኛ ይገናኝ፣ መማር ትርጉም ይኑረው፣ ለሰለጠንበት ሙያ ክብር ይሰጠው፣ ስራ ለመያዝ የኢህዴግ አባልነት መስፈረት አይሁን፣ እውነተኛ ዲሞክራሲ የአገር ህልውና መሰረት ነው ፣ “የምግብ ያለህ፣ የስራ ያለህ፣ የፍትህ ያለህ ፣ የመብራት ያለህ የሚሉት የህዝብ ድምጾች ይሰሙ” የሚሉት ይገኙበታል።

የድርጀቱ ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አገዛዙ ሰልፉ እንዳይካሄድ ለማድረግ የተለያዩ ጫናዎችን ቢፈጥርም ህዝቡ ግን ጫናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ በሰልፉ ላይ በመገኘቱ አመሰግነዋል።