የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አሁንም በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው

ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የተነሳው ግጭት አሁንም አስከፊ በሆነ መልኩ እንደቀጠለ ከአካካቢው የሚደርሱን መረጃዎች አመልክተዋል። የዩኒቨርስቲው ምክትል ዲን ዶ/ር ጨመዳ ችግሩ ከዩኒቨርስቲው አቅም በላይ መሆኑን ለተማሪዎች ተናግረዋል።

ባለፈው አርብ በተማሪዎች መካከል አካባቢን መሰረት አድርጎ በተነሳ ግጭት አንድ ተማሪ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደል አንዲት ሴት ተማሪም እንዲሁ ከፍተኛ የሚባል አካላዊ ጉድለት ደርሶባታል።

በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች መካነ ስላሴ ካቴደራል ተጠልለው ህዝቡ እርዳታ እያደረገላቸው ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ በግለሰቦች ቤት ተጠግተው ይገኛሉ። ከአለማያ ወደ ሃረር ተሳፍረው ለመጓዝ ሙከራ የሚያደርጉ ተማሪዎችም ተይዘው ይደበደባሉ።

በቅርቡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ የፈነዳውን ፈንጅ እንዲሁም በተማሪዎች መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ከ100 በላይ ቁስለኞች  በህይወት ፋና ሆስፒታል ተኝተው በመታከም ላይ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ክትትል በሚደረግበት አይ ሲ ዩ በሚባለው ክፍል ውስጥ 7 ተማሪዎች መገኘታቸውም እንዲሁም፣ ሆዳቸው ፣ ጭንቅላታቸውና እግራቸው ውስጥ የቦንብ ፍንጣሪ ያለባቸው 8 ተማሪዎች በዚሁ ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ።

ለማ የሚባል የአባቱ ስም ያልታወቀ ተማሪም ሆስፒታል ከገባ በሁዋላ በማረፉ አስከሬኑን የሚወስድ ጠፍቶ በአስከሬን ማቆያ ውስጥ እንደሚገኝ የሆስፒታል ምንጮች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኦህዴድ በመካከለኛ ደረጃ ያሉ አመራሮችን ሰብስቦ ሰሞኑን በክልሉ ለታየው ግጭት የሌሎች ብሄር ተወላጆችን ተጠያቄ ማድረጉ ታውቋል።

በስብሰባው የተሳተፉ ምንጫችን እንደገለጹት ኦህዴድ የተማሪዎችን የመብት ጥያቄ የዘር ግጭት አስመስሎ ለማቅረብ መፈለጉ ፣ መንግስት ጉዳዩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው መሆኑን የሚያመለክት ነው። የአህዴድ ካድሬዎች ለተሰብሳቢዎች ” የአንድን ብሄር ስም እየጠሩ፣ ትናንት የገደሉን አንሶ አሁን ደግሞ ይሰድቡናል” በማለት መናገራቸውንና አንዳንድ ካድሬዎችም ይህንኑ በቁጭት ሲናገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ህወሃት በኦህዴድ አማካኝነት እየሄደበት ያለው መንገድ አደገኛ ነው የሚሉት ምንጫችን ፣ ህዝቡ በጊዜ ካልነቃ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችላል በማለት አስጠንቅቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ባወጣው መግለጫ በተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ፣ የደረሰውን የአካል ጉዳትና እስራት አውግዞ፣ አዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ እንዲሁም በተማሪዎች ላይ ግድያ የፈጸሙ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞቸ ፣ ጋዜጠኞችና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋል።