አንድነት በደብደረማርቆስ እና በአዳማ ለሚካሂደው የተቃውሞ ሰልፍ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው

ግንቦት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የድርጅቱ አመራሮች ለኢሳት እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ቀናት በርካታ በራሪ ወረቀቶች ተበትነዋል፣ ፖስተሮችን መለጠፍና በድምጽ ማጉያ መሳሪያ በመጠቀም ቅስቀሳ ተካሂዷል።

የህዝቡ ስሜት አስገራሚ ነው የሚሉት አመራሮች፣ ህዝቡ ወረቀቶችን ያለምንም ችግር እየተቀበለ እንደሚያሰራጭ፣ በተለይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ አመራሮች ገልጸዋል።

የአንድነት ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ሰብሳቢ አቶ ዋለ ባየ በእሁዱ ሰልፍ ብዙ ህዝብ ወጥቶ ተቃውሞውን ይገልጻል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ህዝቡ በከተማው የሚታየውን የተበላሸ መልካም አስተዳደር እና የልማት እጦት ወደ አደባባይ በመውጣት ለመንግስት አካላት ያቀርባል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በአዳማ የሚካሄደው ቅስቀሳም እንዲሁ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። የፓርቲው አመራሮችና ደጋፈዎች በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች እየዞሩ በራሪ ወረቀቶችን ሲበትኑ ውለዋል።

አንድነት የሚሊዮኖች ድምጽ ለመሬት ባለቤትነት በሚል መሪ ቃል ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓም በደብረማርቆስ፣ አዳማ /ናዝሬት፣ በቁጫ/ሰላም በር የተቃውሞ ሰልፍ ያካሂዳል።

አንድነት በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጉ ይታወሳል።