መንግስት በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ቦንብ የወረወሩትን መያዙን አስታወቀ

ግንቦት ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጸር ሽብር ግብረሃይል ለአንድ ተማሪ ህይወት መጥፋትና ከ15 በላይ ተማሪዎች መቁሰል ተጠያቂ የሆኑ ተማሪዎችን በተለያዩ ጊዜ አፈላልጎ መያዙን አስታውቋል።

አበበ ኡርጌሳ፣ ኑረዲን ሃሰን፣ ኒሞና ጫሌና መገርሳ ወርቁ የተባሉት ተማሪዎች ቦንቦን ካፈነዱ በሁዋላ በተማሪዎቹ ላይ በፌሮና በድንጋይ ድብደባ መፈጸማቸውን ግብረሃይሉ ገልጿል።

ኑረዲን ሃሰን የተባለው የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ በእስር ቤት ራሱን ማጥፋቱን መንግስት አክሎ አስታውቋል። ይሁን እንጅ ቀደም ብለው የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ተማሪ ኑረዲን የሞተው በድበደባ ብዛት ሰውነቱ ተጎድቶና ተሰቃይቶ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ቦንብ የወረወሩ ተማሪዎችን ያዝኩ በማለት ወነጀለኛ አድረጎ ቢያቀርባቸውም ፣ ተማሪዎች  ቃላቸውን በገለልተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው እስካልሰጡ ድረስ የመንግስትን መረጃ አምኖ ለመቀበል እንደሚከብድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ በነበረውና ተማሪዎች በጥብቅ ሁኔታ እየተፈተሹ በሚገቡበት ሃሮማያ ዩኒቨርስቲ  ቦንብ እንዴት ሊገባ እንደቻለ አሁንም እንቆቅልሽ ነው።

መንግስት በቅርቡ በኦሮምያ የነበረውን ተቃውሞ አነሳስተዋል በማለት የጠረጠራቸውን ሰዎች ይዞ እያሰረ ነው።