(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2011) የኢትዮ-ቴሌኮም የቀድሞው የኦፕሬሽን ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ዳኘው በአዲስ የሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ።
አቶ ኢሳያስ ዳኘው በሌብነት ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ በዋስ እንዲፈቱ በጠቅላይ ፍርድቤት ተወስኖላቸው እንደነበር ታውቋል።
የሜቴክ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩትና በእስር ላይ የሚገኙት ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ፖሊስና አቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በማመልከታቸው ዋስትና እንዲታገድ መደረጉም ታውቋል።
የከፍተኛው ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀደም ሲል ለአቶ ኢሳያስ ዳኘው በ2 መቶ ሺ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ይህም ዋስ የተፈቀደላቸው ከሐገር የመውጣት መብታቸው እንዲገደብ በማድረግ እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
ይህም ውሳኔ ሲሰጥ ፖሊስ ዋስትና መፍቀድ ትክክል አይደለም በሚል ለላይኛው ይግባኝ በተጨማሪም የፌደራል አቃቢ ሕግ ዋስትናውን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመሳሳይ አቤቱታ ማቅረቡ ታውቋል።
እናም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የፖሊስና የአቃቤ ሕግን ማመልከቻ ተቀብሎ አቶ ኢሳያስ ዳኘው በእስር እንዲቆዩ ወስኖ ነበር።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት በ10 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ውሳኔ በመስጠት ዋስትናውን አግዶ ቢቆይም አቃቤ ሕግ ግን በተባለው ጊዜ ክሱን ለመመስረት አልቻለም።
እናም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዜ አልተከበረም በሚል አቶ ኢሳያስ ዳኘው ዋስትናቸው እንዲፈቀድ በመጨረሻም ውሳኔ አሳለፈ።
አቃቤ ሕግ ክሱን ለመመስረት 15 ተጨማሪ ቀናት ይሰጠኝ ቢልም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ዋስትናውን መፍቀዱ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ፖሊስና አቃቤ ሕግ የቀድሞውን የኢትዮ-ቴሌኮም የኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ዳኘውን በሌላ የሌብነት ወንጀል ጠርጥረናቸዋል ብለው አዲስ ነገር ይዘውባቸው መምጣታቸው ታውቋል።
አቃቤ ሕግና ፖሊስ እንደሚሉት አቶ ኢሳያስ ዳኘው ለ12 ሰልጣኞች በሰአት ከ125 እስከ 150 ዶላር እንዲከፈላቸው በማድረግ ለአንድ ኢዴኡም ለተባለ የአሜሪካ ተቋም ያለጨረታ ስራ ሰጥተዋል።
የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ኢሳያስ በሕገወጥ መንገድ 10 በመቶ ተጨማሪ የመጠባበቂያ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ ከ1 መቶ ሺ ዶላር በላይ መንግስትን ለኪሳራ ዳርገዋል።
ይህም ስራው ሳይጠናቀቅ የተከፈለ የመጠባበቂያ ገንዘብ ነው ተብሏል።
በአዲሱ የፖሊስ ውንጀላ በእስር ላይ እንዲቆዩለትም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቃቤ ሕግ ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቷል።
የአቶ ኢሳያስ ዳኘው ጠበቆች በአዲሱ ውንጀላ ተከፈለ የተባለው ገንዘብ ደንበኛቸው በመንግስት ሃላፊነት ላይ እያሉ የተፈጸመ ቢሆንም በወቅቱ በመስሪያ ቤቱ የቦርድ አመራር አባላት በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በአሁኑ የትግራይ ክልል ምክትል መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ትዕዛዝ የተፈጸመ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ይህም ሆኖ ግን የጠበቆቻቸው ሃሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አቶ ኢሳያስ በቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ተወስኗል።