በኢትዮ-አሜሪካ ለተቋቋሙ የንግድ ሰጪ ተቋማት ድጋፍ ይደረጋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2011)የኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮ-አሜሪካ ለተቋቋሙ የንግድ ሰጪ ተቋማት ድጋፉን እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የንግድ ምክር ቤቱ አባል ለሆኑ ተቋማት በማንኛውም መንግስታዊና ሕጋዊ በሆኑ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የንግድ ማህበረሰቡን ወክሎ የአባላቱን ጥቅም እንደሚያስከብርም ምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል።

ምክር ቤቱ በይፋ መመስረቱ በተገለጸበት መድረክ ላይ ምክር ቤቱ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ድጋፉን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ምስረታ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ መስራችና የጊዜያዊ ቦርዱ ፕሬዝዳንት አቶ አወቀ ስምወርቅ ምክር ቤቱ ሲመሰረት ሁለት አላማዎችን ይዞ ነው ብለዋል በንግግራቸው።

የጋራ ችግሮችን በጋራ መፍታትና ችግሮች እንኳን ባይኖሩ ሁሉም የንግድ ተቋማት የበለጠ ውጤታማና ትርፋማ ሆነው የሚያድጉበትና የሚያስፋፉበትን መንገድ ማመቻቸት አላማዎቹ አላማዎቹ ናቸው ብለዋል።

ለንግድ ማህበረሰቡ ዝርዝር ጥናቶችን ከማቅረብ ጀምሮ ስልጠናዎችን መስጠትና ሌሎች አገልግሎቶችን ማቅረብም የንግድ ምክር ቤቱ ዋነኛ ስራ ነው ብለዋል።

ንግድ ምክር ቤቱ በቨርጂኒያ፣በዋሽንግተን ዲሲ፣በሜሪላንድና በሌሎች አካባቢዎች ለሚገኙ የኢትዮጵያውያን የንግድ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ምክር ቤቱ የመመስረቻ የመጀመሪያ ጉባኤውን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 17/2019 እንደሚያካሂድም ታውቋል።