ኢሳት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና ይገባዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 8/2011)በኢትዮጵያ ለተካሄደው ለውጥ ኢሳት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና እንደሚገባው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ገለጹ።

የኢሳት የጋዜጠኞች ቡድን አዲስ አበባ ሲገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳሁንን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን አቀባበል አድርገውለታል።

የኢሳትን ጋዜጠኞች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋቸዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሳሁን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የኢሳትን ጋዜጠኞች ሲቀበሉ የሚዲያ ተቋሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የይቅርታና የመቻቻል እሴቱ እንዲዳብር ጉልህ ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረጉ ኢሳት ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሒሩት ካሳሁን ገለጻ ኢትዮጵያ የዜጎች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን ማደጊያ መበልጸጊያ ልትሆን ይገባል።

እናም የኢሳት ስራ ለዚሁም ግብ በስፋት መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኢሳት ጋዜጠኞች ቡድንን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

በዚህ ውይይት ላይም አቶ ደመቀ በለውጡ ጉዞ እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎችና እድሎችን ማብራራታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

እናም ኢሳት ለለውጡ ስኬት ሚዛናዊና ገንቢ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢሳት ሚዲያ ቡድን አባላት በበኩላቸው የተጀመረው ለውጥ ዳር እስኪደርስ ድረስ ሚዛናዊና ገንቢ ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የኢሳት የጋዜጠኞች ቡድን አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም በኢትዮጵያ ዋና ጽሕፈት ቤቱን በማድረግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢሳት የጋዜጠኞች ቡድን አዲስ አበባ ሲገባ በርካታ ኢትዮጵያውያን ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ተገኝተው አቀባበል አድርገውለታል።

በነገው እለትም የካቲት 9/2011 ደግሞ በሚሊኒየም አዳራሽ 25ሺ ሕዝብ በተገኘበት ኢሳት ለሃገሬ በሚል ዝግጅት ደማቅ የአቀባበል ስነ ስርአት እንደሚካሄድ ይጠብቃል።