የኦነግ ሰራዊት አባላት ወደ ካምፕ ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት/2011)በትጥቅ ትግል ላይ በጫካ የነበሩ ከ1 ሺህ የሚበልጡ የኦነግ ሰራዊት አባላት ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ ገቡ።

ሕዝቡና የፀጥታ አካላት ባደረጉት ቅንጅታዊ ሥራ ከ1 ሺህ የሚበልጡ የኦነግ ሰራዊት አባላት ሀገራዊ ለውጡን ለመደገፍ ቁርጠኛ በመሆን ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ መግባታቸው ታውቋል።

ፋይል

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ሰራዊት አባላት ጦላይን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል በተዘጋጁ የተለያዩ ካምፖች በመግባት ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸው ተነግሯል።

እነዚህ ወደ ካምፕ የገቡት አባላት በቅርቡ በአባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች እገዛ ኦነግ እና ኦዴፓ ካደረጉት የሰላም ስምምነት ጋር የተያየዙ ስለመሆናቸው የተገለጸ ነገር የለም።

የሰራዊት አባላቱ የተደረገላቸው የሰላም ጥሪና እየታየ ያለው የፖለቲካ ለውጥ ለሃገርና ህዝብ ጥቅም ሲሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የትጥቅ ትግል ማድረጉም ለህዝቡ ስለማይጠቅም ሰላማዊ የትግል መንገድ መምረጣቸውን ነው የገለጹት።

የኦነግ አባላቱ እንዳሉት የትጥቅ ትግልን አማራጭ በማድረግ በሃይል የሚንቀሳቀስ ቡድን አካሄድ ተቀባይነት የለውም።

እናም ለውጡን ለማስቀጠል መናበብና መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት።

የበርካቶች ህይወት ያለፈበትን ለውጥ ማደናቀፍም አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።

ለስልጠና ካምፕ የገቡት የኦነግ ወታደሮች የአንድ ሃገር እድገትን ለማረጋገጥ ሰላም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በትጥቅ ትግል ላይ ለሚገኙ ሌሎች ጓዶቻቸውም ትጥቃቸውን ፈተው ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የጦላይ ስልጠና ማዕከል አስተባባሪ ኮሚሽነር ፀሃይ ነጋሽ  በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት የኦነግ አባላት በህገ መንግስቱ፣ በፌደራሊዝሙና በሃገራዊ ለውጡ ዙሪያ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።