አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን የጸጥታ ሃይሎች መታገታቸውን ተከትሎ የሚሰጡት አስተያየቶች ቀጥለዋል

ሰኔ ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከመላ አገሪቱ የስልክ መልእክቶችን በመደወል ለአቶ አንዳርጋቸው ጀግንነት ድጋፋቸውን የሚገልጹ፣ በእርሱ መታሰር የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰማውን ስሜት የሚገልጹና ስለቀጣዩ ህዝባዊ እርምጃ አስተያየቶችን የሚሰጡ በርካታ የስልክ መልእክቶች ለኢሳት እየደረሱ ነው።

“እድሜየ 50ዎቹ አጋማሽ ነው፣ ከስራ ውየ ስገባ የሰማሁት ዜና አስደንግጦኛል፣ ስሜቴን መቆጣጠርም አልቻልኩም፣ ቤተሰቤን ልጆቼን ትቼ ትግሉን ለመቀላቀል ወስኛለሁ” በማለት የተናገሩት አንድ የመንግስት ሰራተኛ፣ የመን አንዳርጋቸውን መፍታት አለባት ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

“አንድ ቴውድሮስን ልናጣ ነው፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም እግዚዎ በሉ” ያሉ አንድ ሰው፣ የደሴ እና አካባቢው ህዝብ በዜናው መረበሹን እያለቀ ተናገሯል

“የሮመዳንን ጾም በወጉ መጾም አልቻልኩም፣ አባቴ የሞተ ቀን እንኳን እንደዚህ አላዘንኩም” የሚሉት አንዲት ሙስሊም ኢትዮጵያዊ፣ የአቶ አንዳርጋቸውን መታሰር ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮ “ሲጾም ውለው አናፈጥርም ያሉ ቤተሰቦች” መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ሌላ አስተያየት ሰጪ እናት ደግሞ ” እኛ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች እየኖርን፣ ሁኔታው ይቀየራል ብለን አዲስ ተስፋ ስናደረግ ይህ ነገር በመፈጸሙ በጣም እናዝናለን ” ካሉ በሁዋላ፣ በአቶ አንዳርጋቸው ላይ በሚፈጸመው ነገር ሁሉ ዝም ብለው እንደማያዩ አክለዋል።

“የመኖች እንዲያውቁት የምንፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅ የሆነ ህዝብ ያለ መሆኑን ነው” በማለት የገለጸው አንድ ወጣት፣ የመን  በአስቸኳይ እንድትለቀው ጠይቋል። “የመን ያደረገቸው ነገር ህዝቡን ይበልጥ ለትግል የሚያነሳሳ ነው” ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ ፣ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የህዝብ ንዴት ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል