የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በአቶ አንዳርጋቸው መታገት ዙሪያ መግለጫ እያወጡ ነው

ሰኔ ፳፮(ሃያ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአፓ የየመን የጸጥታ ሃይሎች በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የወሰዱትን እርምጃ በጽኑ አውግዞ፣ የአገሪቱ መንግስት በአስቸኳይ እንዲለቀው ጠይቋል።

አንዳርጋቸው በአምባገነኖች ፍርድ ቤት በሽብር ወንጀል ተከሶ ሞት የተፈረደበት በመሆኑ፣ ተላልፎ ቢሰጥ ለከፋ ስቃይና ሞት ሊዳረግ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የአቶ አንዳርጋቸው መታሰር አደገኛ የሆነ አሰራር የሚፈጥር በመሆኑ ድርጊቱ በጽኑ ሊኮነን ይገባዋል ሲል ኢህአፓ አሳስቧል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተነስቶ ድርጊቱን ማውገዝና አቶ አንዳርጋቸው ተላልፎ እንዳይሰጥ ጥረት ማድረግ እንዳለበት ኢህአፓ አክሎ ገልጿል።

ለዲሞክራሲና ለፍትህ የሚደረገው ትግል እንዲህ አይነት አስከፊ እርምጃዎችን በመውሰድ እንደማይቆም ገዢዎች ሊያውቁት ይገባል ሲል መግለጫውን አጠቃሏል።

ሸንጎ ባወጣም መግለጫ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ተላልፎ ቢሰጥ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ሊደርስበት እንደሚችል አስጠንቅቆ፣ “ይህአሳልፎየመስጠትጉዳይተግባራዊእንዳይሆንምኢትዮጵያውያንየፖለቲካና ሰብአዊመብትድርጅቶችእንዲሁም፣የየመንእናአለምአቀፍሰብአዊመብት ተሟጋቾችአስቸኻይጥረትእንዲያደርጉ”ጥሪአስተላልፏል።

“በሀገራችን ውስጥ ያለውን ውስብስብ ችግር መፍታት የሚቻለው ግለሰቦችን በማገትና በማሳገት ወይንም ሊያባራ በማይችል የአመጽ አዙሪት ውስጥ በመሽከርከር ሳይሆን በሆደ ሰፊነት በብሄራዊ መግባባት እና እርቅ ሁሉንም ሀይሎች አሳታፊ የሆነ ስርአት በመፍጠር ሊሆን እንደሚገባው” ሸንጎ አክሎ ገልጿል።