አቶ አንዱአለም አራጌ የመንፈስ መረጋጋት ይታይበታል ተባለ

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እሰከ ትናንት ድረስ ህክምና የተነፈገው የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ  የሆነው አንዱአለም አራጌ፣ ኢብሳ አስፋው በተባለ እስረኛ እንዲደበደብ ከተደረገ በሁዋላ፣ ትናንት እና ዛሬ በጥሩ የመንፈስ መረጋጋት ውስጥ ይገኝ እንደነበር ምንጮች ገልጠዋል።

አሁንም እራሱን እንደሚያመው ይናገራል፣ ይሁን እንጅ የመንፈስ መረጋጋት ይታይበታል ያሉት አንድ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ይፋ የማናደርገው የቃሊቲ እስር ቤት ጠባቂ፣ የህክምና ጥያቄው እስካሁን ድረስ ተቀባይነት አለማግኘቱንም ገልጠዋል።

የእስር  ቤቱ ሃላፊዎች አንዱአለም በተመታበት ቀን ዘር እየጠቀሱ ፣ አለኝ የሚለው ደጋፊ መጥቶ ያትርፈው በማለት ሲናገሩ የሰሙ የእስር ቤቱ የሌላ ብሄር ተወላጆች ሲናደዱ እንደነበር ተናግሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዱአለምን  የደበደበው “ የኢህአዴግ  ማጅራት  መቺ “ ሌላው የ አንድነት አመራር አቶ ናትናኤል መኮንን ወደታሰሩበት ዞን መዛወሩንና ከጎኑ መኝታ ማግኘቱን ዶ/ር ነጋሶ ገልጠዋል።

ኢብሳ አስፋዉ የተባለው ግለሰብ፣ሌላው የ አንድነት አመራር የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንን ወደታሰሩበትና  ሶስት መቶ እስረኞች ወደሚገኙበት  ዞን መለወጡ፣ በናትናኤል ላይም ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዶ/ር ነጋሶ ገልጠዋል።

ጉዳዩ ስላሳሰበን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃለፊ ለሆኑት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ጉዳዩን እንዲከታተሉ ደብዳቤ መጻፋቸውን የገለጡት ዶ/ር ነጋሶ ፣ አምባሳደሩ ግን እስካሁን ድረስ መልስ ሊሰጡዋቸው አለመቻላቸው አንድ ችግር እንዳለ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide