በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ግጭት ሊነሳ ይችላል ፣መንግስት ሰራዊቱን ወደ ከተማ እያስገባ ነው

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያ ውስጥ በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ከፍተኛ ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ፍርሀት ነግሷል፤ መንግስት ሰራዊቱን በገፍ ወደ ዋና ከተማዋ እያስገባ ነው

ባለፉት 8 ሳምንታት ዘወትር አርብ በመቶ ሺ የሚቆጠር ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በአወልያ መስጊድ በመሰባሰብ በነጻነት የማምለክ መብታቸው እንዲከበርላቸው ፣  የሀይማኖት መሪዎቻቸውን በዲሞክራሲያዊ ሁኔታ እራሳቸው እንዲመርጡ እና መንግስት ጣልቃ እንዳይገባባቸው  ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በአወሊያ የሚሰበሰቡ ሙስሊሞች 17 አመራሮችን በመምረጥ ከመንግስት ጋር ንግግር እንዲያድረጉ በወከሉዋቸው መሰረት መሪዎቹ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያይተው ውጤቱን ለመስማት ለየካቲት 26 ቀን 2004 ዓም ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ባለፈው አርብ  ከ150 ሺ በላይ ለሚሆኑ ሙስሊሞች ገልጠዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ እየተበተነ ያለው ወረቀት ግን በሙስሊሞች መካከል ደም አፋሳሽ የሆነ ግጭት ሊነሳ የሚችልበት አደጋ እንዳለ የሚያመለክት ነው። ይህ ማንነቱ ባልታወቀ ሀይል የተጻፈ ማስጠንቀቂያ በስፋት መሰራጨቱ የከተማውን ነዋሪ ብቻ ሳይሆን መንግስትንም ሽብር ላይ ጥሎታል።

ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ የሙስሊም ተወካይ ሁኔታው አስፈሪ ደረጃ እየደረሰ መሆኑን አልሸሸጉም። መንግስት ችግሩን በሰላምና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ወታደሮቹን ወደ አዲስ አበባ በብዛት ማስገባትና ካምፕ ውስጥ ማስፈርን በመምረጥ ችግሩን በአፈና ለመፍታት የፈለገ ይመስላል ብለዋል።

በመበተን ላይ ያለው ወረቅት በመግቢያው ላይ ” እንቅስቃሴያችንን ወደሌላ አቅጣጫ አስይዞ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ መጅሊስና በፊደራል ጉዳዮች ስር የሚገኘው የደህንነት ክፍል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ይላል።

ከአስተማማኝ ምንጮችን ተገኘ ባለው መረጃም ፣ የፌደራሉ መንግስት የደህንነት መስሪያ ቤት በተቻለው መጠን ተቃራኒ ቡድን በመፍጠር ሽኩቻው በህዝብና በህገወጦቹ የመጅሊስ አመራር አባላት መካከል መሆኑ ቀርቶ በሁለቱ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው በሱፊያና በወሀብያ ሙስሊሞች መካከል እንዲሆን እየሰራ ነው ሲል አትቶአል።

መንግስት ሙስሊሙ ህዝብ ያነሳውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካልቻለ እና አሁን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ካላቆመ፣ በአገሪቱዋ ውስጥ ደም አፋሳሽ ግጭት ሊከሰት እንደሚችል እኝሁ የሀይማኖት መሪ አስጠንቅቀዋል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide