ከ40 በላይ መምህራን ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ስራ አትጀምሩም ተብለው ታገዱ

የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ተቃውሞ ያስነሱ ከ40 በላይ መምህራን ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ስራ አትጀምሩም ተብለው ታገዱ፣ መምህራኑ ግን አሻፈረኝ ብለዋል

በሰሜን ጎንደር ዞን በደባርቅ ወረዳ ትምህረት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ባለፈው ሳምንት የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ ከ40 በላይ መምህራን ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ስራ አትጀምሩም ተብለዋል።

የወረዳው መስተዳድር ያቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ አንቀበልም በማለት መምህራን በራሳቸው ጊዜ ማስተማር ቢጀምሩም፣ የወረዳው ባለስልጣናት ግን መምሀራኑ እንዳያስተምሩ አግደዋቸዋል።

መምህራን የጠየቅነው የደሞዝ ይጨመርልን ጥያቄ ነው፣ ይህን ጥያቄ መጠየቅ ደግሞ መብት ነው፣ የስራ ማቆም አድማ ማድረግም ህገመንግስታዊ ሆኖ ሳለ የወረዳው ባለስልጣናት ግን ይቅርታ ካልጠየቃችሁ ስራ አትጀምሩም ብለዋል እኛም ይቅርታ አንጠይቅም፣ ብለን ተፋጠናል ሲሉ አንድ መምህር ለኢሳት ተናግረዋል

መምህሩ እንደሚሉት መምህራኑ የታገዱት ለሌሎች መምህራን መጥፎ አርያ ሆናችሁዋል በሚል ምክንያት ነው። መምህሩ እንደሚሉት ግን ጥያቄው የመላው ኢትዮጵያ መምህራን ጥያቄ እንጅ የደባርቅ መምህራን ብቻ ጥያቄ አድርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የፊታችን ሀሙስ ለመምህራን ጥያቄ መልስ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ፣ በተባለው እለት መልስ ካልሰጠ መምህራኑ ምን እርምጃ እንደሚወስዱ አልታወቀም። ይሁን እንጅ የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጡት ግን በትግራይና በአማራ መምህራን መካከል የአላማ አንድነት ተፈጥሮአል።

ሰሞኑን በጎንደር፣ በጎጃም እና በትግራይ አካባቢ የሚደረገው እንቅስቃሴ ያሰጋው መንግስት መምህራኑን ለመከፋፈል ጥረት እያደረገ መሆኑን መምህራን ይናገራሉ።

አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እንዲዳከም ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ፣ መምህራን መብቶቻቸውን ማስከበር ተስኖአቸው ቆይቷል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide