መስከረም ፳፯(ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ለመንግስት ሰራተኞች እና ለኢህአዴግ አባላት የሚሰጠው የፖለቲካ ስልጠና የዩኒቨርስቲ መምህራንም እንዲወስዱ በመገደዳቸው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን
በቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር እና በአሁኑ የጠ/ሚ የፖሊሲ አማካሪ በአቶ በረከት ስምኦን እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው።
ስልጠናውን የሚወስዱት በታሪክ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሶሺኦሎጂ፣ በጆግራፊ፣ በፊዚክስ እና በመሳሰሉት የትምህርት ዘርፎች የፕሮፌሰርነት ማእረግ ያገኙ፣ የተለያዩ ጥናታዊ ምርምሮችን የሰሩና በሙያው የዶክትሬት ተማሪዎችን ሳይቀር የሚያስተምሩ ናቸው።
ኢሳት ውይይቱን በርቀት በመከታተል ለመረዳት እንደቻለው አቶ በረከት በፌደራሊዝም፣ በታሪክ፣ በሃይማኖትና በኢኮኖሚ ጥያቄዎች ዙሪያ ለአስተማሪዎች ስልጠና ሰጥተዋል።
“ማለባበስ የማይቻለው የብሄረሰቦች ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፣ ሚዲያው በወቅቱ ባይነግረንም ከተፈታ በሁዋላ ‘ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሽማግሌ፣ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በመጨረሻም በመከላከያ ጥረት ሊፈታ ችሎአል’ ይባላል።
በዚህ ከቀጠለ ግጭቶች በአለም ሰላም አስከባሪ ተፈታ ሊባይ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየት ከአስተማሪዎች ተሰንዝሯል። አቶ በረከት በኢትዮጵያ ያለው የፌደራል ስርአት የብሄሮችን ጥያቄ የፈታ መሆኑን፣ ግጭቶች በአፈጻጸም የተነሳ አልፎ አልፎ እንደሚከሰቱ
ተናግረዋል። የመገንጠል ጥያቄ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ቢቀመጥም እስካሁን ወደ ተግባር አልተለወጠም ያሉት አቶ በረከት፣ እስካሁን የመገንጠል ጥያቄ ያቀረበ ሃይል ባለመኖሩ ፈተና ውስጥ አለመግባታቸውን ተናግረዋል።
በእለቱ የዩኒቨርስቲ መምህራኑ ካነሱዋቸው ጥያቄዎች መካከል ” እንደ ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ሁሉ በየቀበሌዉ ሰባዊ መብቶች እየተጣሰ ስለሆነ የሰብዓዊ ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ለምን መብት እንዲያስተምሩ አይመደቡም? የሁሉም ችግሮች እናት
privatization of state ወይም መንግስት የግል ተቋም መሆኑና እየታወቀ ኢህአዴግ ለምን እራሱን አይፈትሽም? ኢህአዴግ የዩኒቨርሲቲ ተማሪችን ስራ ለማስቀጠር አባል ማድረጉ ምን ድረስ ያስጉዘዋል? ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ መሬት ለሱዳን ለምን ተሸጠ?
አማራዎችና አማርኛ ተናጋሪ ኦሮሞዎች ለምን በወረዳና ቀበሌ አስተዳዳሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች እንዲፈናቀሉ ይደረጋል? የአንድ ለአምስት አደረጃጀት እንዴት ግሩፕ መመስረት እንዳለብን ለምናዉቅ የዩኒቨርሲቲ፣ መምህራን በአስገዳጅ መልኩ መጫን ምን ማለት ነዉ?
ኢህአዴግ ከ97 ዓ.ም በኋላ ልማት እንጅ ዴሞክራሲን ወደ ጎን ለምን ተወ? ህዝቡን እንደዚህ አናክሳችሁ ኢህአዴግ በድንገት ስልጣን ቢለቅ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነዉ ? የሚሉት ይገኙበታል። ኢህአዴግ ልማታዊ ብሄርተኝነት እንጅ ልማታዊ መንግስት አይደለም”
የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል።
በተመሳሳይ ዜና በአዲስ አበባ በሚካሄደው የኢህአዴግ የፖለቲካ ስልጠና መድረክ ላይ ከተሳታፊዎች ለመድረክ አወያዮች የሚቀርቡት ጥያቄዎች ተጠናክረው እንደቀጠሉ ነው፡፡
ኢህአዴግ በአዲስ አበባ የድርጅት አባላቱን ከአዲስ አመት በፊትና በኋላ ለ13 ቀናት በመጀመሪያ ዙር ካሰለጠነ በኋላ፣ ለሁለተኛ ዙር ደግሞ ለ11 ቀናት በሚቆይ ጊዜ ጥቂት ያልሰለጠኑ አባላትን እና መላ አባል ያልሆኑትን የመንግስት ሠራተኞች ማሰልጠን ከጀመረ
አንድ ሳምንት ተቆጥሯል። ለአዲስ አበባ መስተዳደር ተጠሪ መ/ቤት ሠራተኞች በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ መለስተኛ አዳራሽ፣በሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት አዳራሽ እና ለፌደራል ተጠሪ መ/ቤት የመንግስት ሠራተኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት
ግቢ ውስጥ እዚያው እያደሩና እየሰለጠኑ የሚገኝ ሲሆን ከስልጠናው ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ለተሳታፊዎች የሚያስፈልጋቸውን አበል በስልጠናው አጋማሽ ላይ ለላኳቸው መ/ቤቶች ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ቀጥታ ስልክ በመደወል ከመንግስት
ካዝና በአስቸኳይ አበል እንዲዘጋጅላቸውና ክፍያ እንዲከፈል የተደረገ ሲሆን፤ በመቀጠል በሁሉም የስልጠና ቦታዎች ከስልጠናው ተሳታፊ የመንግስት ሠራተኞች የሚቀርበው ጥያቄ ለኢህአዴግ አወያይ ካድሬዎች ከአቅም በላይ እንደሆነባቸውም ለማዎቅ ተችሏል፡፡
አንዳንድ የስልጠናው ተሳታፊዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ከስልጠናው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተመጣጣኝ ምላሽ ሳይሰጥ እዚያው በስብሰባው ላይ በተዘጋጀው የ1 ለ 5 ቡድን ላይ በጋራ ተወያዩበት እያለ እንደሚገኝ እና በዚሁ የ1 ለ 5 ቡድን ላይም እርስ በርሳቸው
እንዲገማገሙ በማድረግ በስብሰባው ላይ ንቁ ተሳታፊ ለሆነ ጥሩ ነጥብ፣ ንቁ ተሳታፊ ላልሆነ ደግሞ ዝቅተኛ ነጥብ እንዲሰጥ እያደረገ ነው። ኢህአዴግ በስልጠና በመድረኮቹ ላይ ትኩረት ያደረገው ከተሳታፊዎቹ በተናጠል ለሚነሱ ጥያቄዎች እንጂ ለሚመለሰው
መልስ እንዳልሆነ ለማዎቅ ተችሎአል፡፡ በተሳታፊዎች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል “ኢህአዴግ ራሱን ብቻ ታሪክ ሰሪ አድርጎ የሌሎቹን መንግስታት ታሪክ እንዲጠፋ ይፈልጋል፤ ህዝቡን እንደማያቅ በመቁጠር ነፃ ጋዜጦችን በስበብ አስባብ ከገበያ በማስወጣት ህዝቡ
የደርጅቱን ታማኝ ፕሬሶች ብቻ እንዲከታተል እያደረጋችሁ ነው፤ እንዴት አንድ እንኳ ነፃ ጋዜጣ እንዲኖር አታደርጉም፤የሃይማኖት እኩልነት አለ እያለችሁ፣ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ እጁን አላስገባም እያላችሁ በተግባር ግን ሲታይ ከእጃችሁ አልፎ መላ
አካላታችሁ በተለይ በእስልማነ ሃይማኖት ውስጥ በግልጽ አስገብታችኋል፤ መስኪዶችን በጠራራ ጸሃይ ታሽጋላችሁ፤ የፌደራል ልዩ ሃይል ፖሊሶች የሚመሩበት ህግ አለ ወይ? የትምህርት ፖሊሲውን አጥፍታችሁታል፤ ለይስሙላ ምርጫ ብላችሁ ብዙ ሃብት
ከምታባክኑ ወደ ለየለት ጭቆና ብትገቡ አይሻልም ወይ፤ እናንተ በመጣችሁበት መንገድ በታጣቂ ሃይል ካልሆነ በስተቀር በምርጫ የምትለቁ አይመስልም፤ እናንተ የምትመሩበት የፖለቲካ ርእዮት አለም ግልጽ ሳይሆን የምዕራባዊያንን የፖለቲካ ሪዕዮትአለም
በጅምላ ታጥላላችሁ” የሚሉት ይገኙበታል።