አቶ ሽመልስ ከማል ዳግም ተጋለጡ

ሐምሌ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመንግስት ቃል አቀባይ ነኝ የሚሉት አቶ ሽመልስ ከማል ስካይፒንና ሌሎችን የኢንተርኔት የመገናኛ ዘዴዎችን የሚከለክል ህግ አላወጣንም በማለት አለም የሚያውቀውን ሀቅ ሲክዱ ቢቆዩም፣ ትናንት ቃል በሚያቀብሉለት መንግስት ተጋልጠዋል።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፓርላማ በትናንት ሃምሌ 4 ቀን 2004 ዓ.ም ውሎው ያፀደቀው ይህ አዲስ አዋጅ፣ ቀደም ሲል የወጣውን አፋኝ ሕግ ሙሉ ለሙሉ የሚሰርዝና፣ የድምጽና የፋክስ መልዕክትን ጨምሮ ስካይፒና ጎግል ቶክን መጠቀም የሚያስችል እንደሆነ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ገልጠዋል።

እንደሚታወቀው በኢንተርኔት አማካኝነት የሚደረጉ የስልክ ግንኙነቶችን የሚከለክለው ሕግ፤ በስካይፒ፣ በያሁ መሴንጄር እና በጎግል ቶክ ጥሪ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ የሚቀበሉትም ከወንጀለኛ ተፈርጀው እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጡ የሚደነግግ ነው።

ይህንኑ በመቃወም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ታዋቂ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ እንዲሁም ሰፊ ስርጭት ያላቸው ታላላቅ የመገናኛ ብዙሃን፣ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት   በሕወሃት/ኢሕአዴግ ስርዓት ላይ ቀላል የማይባል ነቀፋና ትችት እንደሰነዘሩበት ይታወሳል።

ከሁሉም የሚገርመው ነገር የሕወሃት/ኢሓዴግ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ከ15 ቀናት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ መንግስት የስካይፒ ጥሪንም ሆነ በጎግል እና በያሁ የሚደረጉ የድምጽ ጥሪዎችን የሚያግድ ሕግ አላወጣም” በማለት መንግስት አሁን በግልጽ ሽሬዋለሁ የሚለውን አዋጅ እንዳላወጣ ለማስተባበል መሞከራቸው ነበር።

እርሳቸው ይህን መግለጫ በሰጡ በሁለተኛው ቀን  አቶ በረከት ስምኦን፣ “ኢንተርኔት ለቴሌኮም አገልግሎት የመጠቀም ተግባር አገሪቱን ከፍተኛ ገቢ እያሳጣት በመምጣቱ ስካይፒን ጨምሮ ሌሎች የኢንተርኔት የቴሌኮም አገልግሎቶችን መንግስት ለመዝጋት ወስኗል” ማለታቸው ይታወሳል።

አቶ ሽመልስ፣ ብዙ ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ  ሌሎች የሕወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት በግልጽ የተናገሩትንና ሕዝብ የሚያውቀውን እውነታ ሽምጥጥ አድርገው በመካድ ለማስተባበል ሲሞክሩ ስለሚታዩ፣ በርካታ ሰዎች “እርሳቸው የመንግስት ቃል አቀባይ ሳይሆኑ ቃለ-አባይ መባል ነው የሚገባቸው” በማለት ይተቿቸዋል።

አቶ ሽመልስ ከዚህ ቀደም የኢህአዴግ መንግስት ዲሞክራሲያዊ ባህሪው ሬዲዮ ለማፈን አይፈቅድለትም ብለው ከተናገሩ በሁዋላ ፣ አቶ መለስ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአሜሪካንን ድምጽ አፍነነዋል በማለት አቶ ሽመልስን የሚያሸማቅቅ ንግግር መናገራቸው ይታወሳል። አቶ ሽመልስ ከማል የሚሰጡት መግለጫ ለኢህአዴግ ሰዎችም አሳፋሪ እየሆነ መጥቷል በማለት ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide