የምርጫ ቦርዱ አቶ ተስፋዬ መንገሻ ከሃላፊነት ተነሱ

ሐምሌ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሐፊ በመሆን ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ ውለታ የዋሉት አቶ ተስፋዬ መንገሻ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ በተለይ ኢህአዴግ በ1997ቱ ምርጫ ከፍተኛ ሸንፈት ባጋጠመው የጭንቀቱ ወቅት በምርጫ ቦርዱ የተቀነባበረ ማጭበርበር በማድረግ፣በድጋሚ ምርጫዎች በቶ በመቶ የተሸነፉ ባለሥልጣናትን በአስደናቂ ሁኔታ መቶ በመቶ  እንዲያሸንፉ በማድረግ  ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡

ከምርጫ 97 በኃላ ለጊዜው ምንነቱ ባልታወቀ ሕመም ሲሰቃዩ ከቆዩ በኃላ በ2002 አገራዊ ምርጫ በከዘራ ጭምር እየታገዙ ኢህአዴግ 99.9 በሆነ ውጤት እንዲያሸንፍ በማድረግ ጮቤ ያሰረገጡ ባለውለታ ናቸው፡፡

ምርጫ ቦርዱ አቶ ተስፋዬን ከኃላፊነታቸው በምን ምክንያት እንዳነሳ ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም ለቦርዱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደጠቆሙት የሰውየው ጤንነት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሸቆለቆለ በመምጣቱና ሥራቸውን በብቃት እንዲሰሩ ባለማስቻሉ ነው፡፡

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በደብዳቤ ፓርላማው የቦርዱን ዋና ጸሐፊና ምክትል ዋና ጸሐፊ ሹመት እንዲያጸድቅላቸው በጠየቁት መሰረት ትላንት ፓርላማው ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሹመቱን ተቀብሎ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡በዚሁ መሰረት አቶ ነጋ ዱፊሳ ዋና ጸሐፊ፣አቶ ወንድሙ ጎላ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

ተሿሚዎቹ ከዚህ ቀደምም በቦርዱ ሥር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ኃላፊነት ያገለገሉ ናቸው፡፡

የመድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ተሿሚዎቹ ቀደም ሲል በቦርዱ በተለያየ ኃላፊነት ቦታ ያገለገሉ በመሆናቸው ነጻና ገለልተኛ ሊሆኑ አይችሉም በሚል ሹመታቸውን ተቃውመዋል፡፡

መድረክ  ከሳምንት በፊት በጠ/ሚኒስትሩ አቅራቢነት የተሾሙት የምርጫ ቦርድ አባላት  በተመሳሳይ ሁኔታ መቃወሙ አይዘነጋም።

አቶ ተስፋየ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሀዊ ምርጫ እንዳይደረግ፣ ዲሞክራሲ እንዳያብብ በማድረግ ከሚወነጀሉ ሰዎች መካከል  መካከል በግንባር ቀደምነት የጠቀሳሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide