ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ዙሪያ ለዓለም ባንክ ደብዳቤ ጻፈ

ሐምሌ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የዓለም ባንክ፤ ኢትዮጵያ   ወደ ኬንያ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት  በሚል እየሰራች ላለው  የአሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ገንዘብ ከመለገሱ በፊት፤ የፕሮጀክቱ  አካባቢው እንዳማይጎዳና  የነዋሪዎች  ህይወት  እንደማይናጋ ሊያረጋግጥ ይገባል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች አሣሰበ።

ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህን ያለው፤ ጎዳዩን አስመልክቶ  ትናንት ለዓለም ባንክ  ፕሬዚዳንት ለጂም ዮንግ ኪም በፃፈው ደብዳቤ ላይ ነው።

የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ፕሮጀክቱን  አስመልክቶ  እየተነሳ ባለው ጥያቄ ዙሪያ ለመነጋገር  በዛሬው ዕለት ስብሰባ ይቀመጣሉ።

ይህ  በዓለም ባንክ የሚደገፍ ፕሮጀክት፤ ከህዝቦቿ 80 በመቶ ያህሉ የ አሌክትሪክ አገልግሎት ለማያገኙት ለኬኒያ ያለው ጠቀሜታ እጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ይሁንና  ባንኩ ፕሮጀክቱን ሲደግፍ፤ በፕሮጀክቱ ምክንያት በአካባቢ እና በነዋሪዎች ላይ ችግር እንዳይከሰት የሚረዱ የጥንቃቄ  ሥራዎች አብረው እንዲከናወኑ በማድረግ በኩል ለሚነሱበት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን መቆየቱን ቁመዋል።

ኢትዮጵያ፤ የ 1000 ኪሎ ሜትር  የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሥራን በማጠናቀቅ ፤በ2014  ወደ ኬኒያ ሀይል የማስተላለፍ ሥራ ለመጀመር ማቀዷን አስታውቃለች።

ይሁንና በዋነኝነት በግልገል ጊቤ ሦስት ላይ የተመሰረተው ይህ እቅድ በአካባቢ ተንከባካቢዎች እና በሰብዓዊ መብት ተማጋቾች ዘንድ ከፍ ያለ ተቃውሞ እያስነሳ ይገኛል።

በሂዩማን ራይትስ ዎች  የ ዓለማቀፍ ፋይናንስ ተቋማት ጠበቃ የሆኑት ጄሲካ ኢቫንስ፦” በግልገል ጊቤ ሦስት  ፕሮጀክት ምክንያት ደህንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ለሚገኙት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።

በ ኦሞ ወንዝ ላይ እየገነባ ያለው ግልገል ጊቤ ቁጥር ሶስት ፕሮጀክት  በሚያመነጨው ሀይል ፤   በ245 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የታገዘ የስኳር ልማት  ተክል ለማካሄድ ማቀዱም ተመልክቷል።

ሆኖም፤የስኳር አገዳ ተክሉ  በታችኛው ኦሞ አካባቢ በሚኖሩ 200 ሺህ የ አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከወዲሁ አደጋ መፍጠሩን ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠቁሟል።

ከዚህም ባሻገር ይህ የግድብ ሥራና  በኢትዮጵያ መንግስት  እየተሰሩ ያሉ ተዛማጅ የእርሻ ፕሮጅክቶች በሚያስገርም ሁኔታ ወደ ኬንያ- የቱርካና ሀይቅ  ይፈስ የነበረውን የውሀ መጠን እንደቀነሱት ድርጅቱ ገልጿል።

እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ደብዳቤ፤የቱርካና ሀይቅ 90 በመቶ የሚሆነውን ውሀ የሚያገኘው ከኦሞ ወንዝ ነው።

ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ፤በቱርካና ሀይቅ ዙሪያ በሚገኙና  ኑሯቸውን በሀይቁ ላይ በመሰረቱ  300 ሺህ ነዋሪዎች  ህይወት ላይ አደጋ እንደሚፈጠር ድርጅቱ ከወዲሁ አሣስቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ  በርካታ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች  ተመሣሳይ ስጋታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

ኪም 12ኛው የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ባለፈው ጁላይ 1 ነው።

“ያቀረብነው ጥያቄ፤ ኪም ለሰብዓዊ መብት እና ለአካባቢ መጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት የምናይበት የመጀመሪያው ትልቅ ፈተና ይሆናል” ብለዋል- ጃሲካ ኢቫንስ።___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide