አርሶ አደሮች በማዳበሪያ እና በምርጥ ዘር እዳ እየተዋከቡ ነው።

ጥቅምት ፳፩(ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በደቡብ እና በአማራ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮቹ ለኢሳት እንደተናገሩት ውጤታማ ባልሆኑበትና በግዴታ እንዲገዙ በተጠየቁት የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ እዳ እየተዋከቡ ነው። እዳችንን መክፈል አልቻንም የሚሉት አርሶ አደሮች መንግስት መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

ግብርና ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የዋለውን ዳፕ የተባለውን ማዳበሪያ ውጤታማ አልሆነም በሚል እንደሚቀይር ማስታወቁ ይታወቃል።

ይሁን እንጅ አርሶአደሮቹ ውጤታማ አልሆነም ለተባለው ማዳበሪያ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ይቃወማሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የገዢውን ፓርቲ ፖለቲካ እንድንማር በመገደዳችን ስራ መስራት አልቻልንም ሲሉ አማረዋል። ሰሞኑን ለአርሶ አደሩ የተሰጠውን የ7 ቀናት የፖለቲካ ስልጠና በማስመልከት እንደተናገሩት፣ ነጋ ጠባ የካድሬዎች ስብሰባ በስራችን ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ኢህአዴግ በቅርቡ በ2005 ዓም  የግብርና ምርት ውጤት መንግስት ካቀደው በታች መሆኑን ገልጾ ነበር።