(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2010)
መንግስት ክሳቸውን ሰርዞ እፈታቸዋለሁ ካላቸው 115 እስረኞች መካከል 4ቱ ችሎት ቀረበው እንደተፈረደባቸው ታወቀ።
ይፈታሉ ተብሎ ስማቸው ከተጠራውና ለስልጠና ወደ ቃልቲ ተውሰደ ከነበሩት 115 እስረኞች መካከል እንደነበሩም ታውቋል።
ነገ ግን ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት እነዚሁ ክሳቸው ተነስቶላቸዋል የተባሉት 4 ተከሳሾች ቀርበው የተላለፈባቸውን ፍርድ እንዲሰሙ መደረጉ ታውቋል።
የህግ ባለሙያዎች በበኩላቸው እንዲህ አይነቱ አካሄድ በዛች ሀገር አዛዥና ታዛዥ መጥፋቱን ብሎም በመንግስት ተቋማት መካከል አለመግባባት መኖሩን ያሳያል ነው ያሉት።
አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሳምንታትን የፈጀ ስብሰባ ካደረጉና ለብሔራዊ መግባባት ሲባል እስረኞች ይፈታሉ ብሎ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ክሳቸው ተሰርዞ በፌደራል ደረጃ ከተባሉት ታሳሪዎች መካከል 115 እስረኞች ይገኙበታል።
ዛሬ ላይ በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የተፈጠረው ነገር ግን ጭራሹኑ የሕወሃት አገዛዝን በውሸት የተሞላ አሰራር ያረገገጠ ነው ተብሏል።
ነገሩ እንዲህ ነው በመንግስት ክሳቸው ተሰርዞ ይፈታሉ የተባሉት የፌደራሉ 115 እስረኞች ወደ ቃሊቲ ተወስደው ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።
ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ሉሉ መሰለ፣ በጋሻው ዱንጋ፣ መርደኪዮስ ሽብሩ እና ጌታሁን ቀጶ ይገኙበታል።
እነዚህ ታሳሪዎች ታዲያ ትፈታላችሁ ከመባልም አልፈው በአገዛዙ እንዲሰጣቸው የተወሰነውን ተሃድሶም ተሳትፈዋል።
ዛሬ ጥር 16/2010 ላይ ግን ከቃሊቲ እንዲመጡ ከተደረገ በኋላ ልደታ ላይ በተሰየመው ችሎት ፊት ቀርበው ከቤተሰባችሁ ጋር ተቀላቀሉ የሚል ዜናን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ከችሎቱ የተሰጣቸው ምላሽ ግን ሌላ ሆኗል።
በተከሰሳችሁበት ወንጀል ፍርድ ተላልፎባችኋል የሚል።
በዚሁም የፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ሉሉ መሰለ 4አመት ከ5 ወር፣ በጋሻው ዱንጋ 4አመት ከ5 ወር፣ ጌታሁን ቀጶ 5 አመት ከ10 ወር እንዲሁም መርደኪዮስ ሽብሩ 5 አመት ተፈርዶባቸዋል።
እስረኞቹም ፍርዱን ከሰሙ በኋላ እኛኮ ከተፈቺዎቹ መካከል ነን የሚል ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ ቢያቀርቡም ከችሎቱ የተሰጣቸው ምላሽ ግን ጉዳያችሁን ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር ጨርሱ የሚል ነው።
ጌታቸው ሽፈራው በመራጃ መረቡ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ በእነ ሉሉ መሰለ የክስ መዝገብ ላይ የተፈጠረው ይሄ ብቻ አይደለም ይላል።
ይፈታሉ ከተባሉትና “ተሃድሶ” ወስደው ከተፈረደባቸው በተጨማሪ ይፈታሉ ከተባሉት 115 እስረኞች መካከል ያልተፈቱ ሌሎች እስረኞችም እንዳሉ አስቀምጧል።
በእነ ትንሳኤ በሪሶ የክስ መዝገብ 7ኛ ተከሳሽ አሰጋ አሰፋ፣ 8ኛ ተከሳሽ ጌታቸው ይርጋና 9ኛ ተከሳሽ ዳኛ ሽቴ ሙሉ መዝገባቸው ጠፍቷል በሚል አልተፈቱም ብሏል።
የህግ ባለሙያዎች ይህን የፍርድ ቤት ሂደት አስገራሚና አስደናቂ ሲሉ ነው የገለጹት።
ተከሳሶቹ ይፈታሉ የተባለው ከፍርድ በፊት ክሳቸው እንዲነሳ ተደርጎ ነው።
አስቀድሞ ጥፋተኛ ከተባሉ ግን እንዴት ክሳቸው ሊነሳ ይችላል ሲሉም ከህግ አግባብ ይጠይቃሉ።
አሁን ላይ ነገሩ ተወሳስቧል ግራ የገባውንና በቃሉ መገኘት የማይችለውን የሕወሃት አገዛዝ በዚህ ውስጥ ማየት ይቻላል ብለዋል።
ከዚህም ሌላ ተቋማት እርስ በርሳቸው እንደማይገባቡና አዛዥና ታዛዥ የጠፋበት አካሄድ መሆኑን በግልጽ ያስቀመጠ ነው ይላሉ።
ፍርድ ቤት ያጸደቀውን ጉዳይ አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ፖሊስ ሲሽረው የታየበትን አጋጣሚ በማሳያነትም ያነሳሉ።
አሁን ላይ እየታዩ ያሉት ልዩነቶች የፍትህ ተቋማቱ ስርአት አልበኝነት እየሰፈነባቸው መምጣቱን በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።