በመተማ ከተማ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2010)

በሰሜን ጎንደር ዞን መተማ ከተማ የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ።

ትላንት ምሽት በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት የህወሃት አባል በሆነ ግለሰብ ሆቴል ላይም ጉዳት መደረሱን ለማወቅ ተችሏል።

በሆቴሉ የህወሃት አገዛዝ የቀጠናው የደህንነት ሃላፊዎች ስብሰባ ያደርጉ ነበር ተብሏል።

በተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የከተማዋ ሁለት ባለስልጣናት ወደ ጎንደር ሆስፒታል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ባልታወቁ ሃይሎች የተፈጸመውን ይህን ጥቃት በተመለከተ በመንግስት በኩል የተባለ ነገር የለም።

አዲስ ዘመን ሆቴል በመተማ ይገኛል።

የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት የዚህ ሆቴል ባለቤት የህወሃት የደህንነት አባል ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ እስከ ሱዳን የድንበር ከተሞችና በኤርትራ የወሰን መንደሮች እየዘለቁ የደህንነትና የስለላ ስራ የሚያከናወኑ፣ የሚያፍኑና የሚገድሉ የህወሀት የደህንነት ሰዎች በብዛት የሚያዘወትሩበት ሆቴል እንደሆነ ይነገራል።

የድንበር አካባቢና የሰሜን ምዕራብ የደህንነት ሃላፊ አቶ ጉዑሽ፣ የመተማ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ እንዲሁም የቀጠናው የኮማንድ ፖስት አዛዥ ትላንት ምሽት በዚህ ሆቴል ስብሰባ ነበራቸው።

ይህ መረጃ የደረሳቸው ማንነታቸው ያልታወቁ ሃይሎች ለጥቃት ዕቅድ አውጥተው መዘጋጀታቸውን ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የሚገለጹት።

በዕቅዱ መሰረትም በተጠቀሰው ሆቴል የቦምብ ጥቃት ተፈጽሟል።

እንደ ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሁለት ሰዓት የተፈጸመው ጥቃት ዒላማ ያደረገው የቀጠናው የደህንነትና የጸጥታ አመራሮች ላይ ነበር።

ከሶስቱ ዋና ዋና አመራሮች ሁለቱ በተፈጸመው ጥቃት በጽኑ መቁሰላቸው የተገለጸ ሲሆን ለከፍተኛ ህክምና ወደ ጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በጥቃቱ የተገደሉ እንዳሉም የሚያመለክቱ መረጃዎች ቢወጡም ኢሳት ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ጥቃቱን የፈጸሙት ሃይሎች የወልዲያውን ጭፍጭፋ ለመበቀል በሚል እንዳደረጉት የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል ትላንት በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ አቅራቢያ በምትገኘው ሀራ ከተማ በኩል ለመከላከያ ሰራዊት ነዳጅ ለማቅረብ ሲጓዝ በነበረ ቦቴ ከባድ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ መውደሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከቦቴው ተሽከርካሪ ሌላ ደረቅ ራሽን ምግብ ለሰራዊቱ ሲያጓጉዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይም ጥቃት ተሰንዝሮ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን መደረጉ ታውቋል።

ወደትግራይ የሚወስደው መንገድ ዝግ ሆኖ እንደቀጠለ መሆኑን የሚገልጹ ምንጮች ውጥረቱ እየተባባሰ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም በቆቦ የህዝብ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦች ንብረት ላይ ርምጃ መወሰዱን ተከትሎ የአጋዚ ሰራዊት ተኩስ መከፍቱ ተሰምቷል።

የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደደረሰን እናቀርባለን።