በወልቂጤ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ዛሬ የተካሄደው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ቢጀመርም ልዩ ሃይል ሰዎችን ማሰሩን ተከትሎ ወደ ግጭት መቀየሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በወልቂጤ ከተማ ሊገነባ የመሰረት ድንጋይ የተጣለለት ሆስፒታል ፕሮጀክት ወደ ትግራይ ተወስዷል የሚል መረጃ ህዝቡ ዘንድ መድረሱ ለተቃውሞው መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ትርቃለች።

ወደ ጅማ በሚወስደው መንገድ ላይ ከሚገኙ ከተሞች ትልቋ እንደሆነች ይነገራል።

በህወሀት አገዛዝ በተሰመረው የክልል ወሰን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ስር ስትሆን የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በመሆን ትጠቀሳለች–ወልቂጤ።

የ1997ቱ ምርጫ ውጤት ለህወሃት አገዛዝ ከፍተኛ ሽንፈት ካከናነቡ አካባቢዎች ወልቂጤ አንዷ ናት።

ይህም በአገዛዙ በኩርኩም እንድትመታ፣ በልማትና መልካም አስተዳደር የኋልዮሽ እንድትጓዝ ተፈርዶባታል ይላሉ የአካባቢው ተወላጆች።

የቂም በቀል በትር ያረፈባት ወልቂጤ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የነዋሪዋ ብሶትና በደል እየተባባሰ እንደመጣ ያነጋገርናቸው ይገልጻሉ።

አልፎ አልፎ ህዝቡ ቁጣውን የሚያሳይበት አጋጣሚ የተፈጠረ ቢሆንም በአገዛዙ የአፈና ርምጃ የህዝቡ በደልና ስቃይ እንዲዳፈን ሆኗል።

ዛሬ ግን ትዕግስታችን አለቀ ነው ያለው የወልቂጤ ነዋሪ።

በተለይም ለከተማዋ የታቀደውና በውጭ እርዳታ ይሰራል የተባለው ዘመናዊ ግዙፍ ሆስፒታል የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ የነዋሪውን ቁጣ ለአደባባይ እንዲበቃ አድርጎታል።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ እንደተመለከተው እንደ ኢትዮጵያኑ አቆጣጠር በ2007 የመሰረት ድንጋይ የተጣለለትና በዓይነቱ በኢትዮጵያ ትልቅና ዘመናዊ ይሆናል የተባለው ሆስፒታል ግንባታው ሳይጀመር ከሶስት ዓመት በላይ መቆየቱ ለወልቂጤ ነዋሪ ቁጣውን ለመግለጽ ከበቂ በላይ ምክንያት ነበር።

በተደጋጋሚ ለጉራጌ ዞንና ለወልቂጤ ከተማ ባለስልጣናት ጉዳዩን አንስተው መጠየቃቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች ምላሽ የሚሰጥ አላገኙም።

ትዕግስታችን በመሟጠጡ ዛሬ ቁጣችንንና ብሶታችንን ለማሰማት አደባባይ ወተናል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በተለይም የሆስፒታሉ ፕሮጀክት እንዳለ ወደ ትግራይ ተዛውሯል የሚል መረጃ ህዝቡ ውስጥ መሰራጨቱ ለዛሬው ተቃውሞ መነሻ መሆኑ ይነገራል።

ኢሳት የተባለው መረጃ ትክክለኝነትን ለማጣራት ያደረገው ጥረትም አልተሳካለትም።

በህዝቡ ዘንድ በሰፊው እንደሚነገረው የሆስፒታሉ ግንባታ ወደትግራይ በመዞሩ በወልቂጤ የታቀደው ቀርቷል።

ይህም ህዝቡን በቁጣ እንዲወጣ አድርጎታል ተብሏል።

የኢሳት ወኪል ከስፍራው እንደገለጸው በተደራራቢ በደል እየተሰቃየ የከረመው የወልቂጤ ነዋሪ ቁጣውን በሰላማዊ መንገድ እየገለጸ በነበረበት ጊዜ የልዩ ሃይል አባላት ከሰልፈኞቹ መሃል አንዳንዶችን እያፈኑ መውሰዳቸው ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል።

የታሰሩትን ለማስፈታት ህዝቡ ድንጋይ በመወርወርና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ከልዩ ሃይል ጋር ግብግብ የገጠሙ ሲሆን ፖሊስም አስለቃሽ ጢስ መጠቀሙ ታውቋል።

የህዝቡ ተቃውሞ እየበረታ በመሄዱም የተወሰኑት ታሳሪዎች መለቀቃቸው ታውቋል።

ሆኖም ተቃውሞው ቀጥሎ መንገድ በመዝጋት የልዩ ሃይልና የመንግስት ተሽከርካሪዎችን መስታወቶች በመሰባበር ግጭቱ መቀጠሉን ያገነኘው መረጃ ያመለክታል።

ሱቆች መደብሮች የንግድ ቦታዎች ተዘግተው የነበረ ሲሆን ከአዲስ አበባና ከጅማ የሚያስገቡ መንገዶችም አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ ተገልጿል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በአስቸኳይ የማይጀመር ከሆነ አጠቃላይ ህዝባዊ አመጽ የሚጠራ መሆኑን ነዋሪው አስጠንቅቋል።

በዕለቱ የደረሰ የከፋ ጉዳት እንደሌለ ታውቋል። ስለዕለቱ ተቃውሞ ከአካባቢው የመንግስት ባልስልጣናት የተሰጠ ምላሽ የለም።