ህዝብን በመጨፍጨፍ ትግሉን ለመቀልበስ አይቻልም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2010)

ህዝብን በመጨፍጨፍ ትግሉን ለመቀልበስ አይቻልም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በወልዲያ በህወህት ታጣቂዎች የተፈጸመውን ግድያ አወገዘ ።

ትግሉን ከአሁኑ በተሻለ ህዝቡና ታጋይ ሃይሎች አዲስ መርሀግብር በመንድፈ በጋራ መታገል ይኖርብናል በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብቶች ሊግ በወልዲያ የተፈጸመውን ጥቃት ትውልድ ላይ የተቃጣ ብሔራዊነትን አደጋ ላይ የጣለ ሲል መግለጫ አውጥቷል።

የ2010 የጥምቀት በዓል በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል አንድነትን የሰበከ፣የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ ያደረገ፣አገዛዙን የሚቃወሙ ድምጾች የተስተጋቡበት ከዛ አልፎ መሪር ሀዘን የታየበትና የተሰማበት ሆኖ አልፏል።

በወልዲያ በቃና ዘገሊላ የሚካኤል በዓል ላይ የተፈጸመው ግድያ ብዙዎችን የሀዘን ማቅ አልብሷል። ከ10 በላይ ለተገደሉብት ጭፍጨፋ የስርዓቱ ባለስልጣናት የከተማን ወጣቶች ተጠያቂ ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ህዝቡን ይበለጥ አስቆጥቷል።

የከተማው ህዝብ የአገዛዙ ደጋፊና ቅርብ ናቸው የተባሉትን በመነጠል ርምጃ መውሰዱንም ቀጥሏል።

በወልዲያ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፣የሲቪክ ማህበራት፣የፓለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች ግድያውን በማውገዝ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋር ትግል ሸንጎ ግድያውን በማውገዝ ህዝብን በመጨፍጨፍ ህወሃት መራሹ፣ አፋኙና ዘረኛው አገዛዝ የፖለቲካ ምህዳሩን አሰፋለሁ፣ ሕዝብን አደምጣለሁ ባለ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወጣቶችን በአደባባይ በመረሸን የማይለወጥ ማንነቱን አሳይቷል።

መግለጫው እንደሚለው አገዛዙ የማይሰማና ከስህተቱም ሆነ ከታሪክ የማይማር ነው።

ስለዚህም ህዝብን በመግደልና በማሰር ትግሉን መቀልበስ አይቻልም ይላል መግለጫው።

ትግሉን ከአሁኑ በተሻለ ተደረጅቶ፣ህዝቡና ታጋይ ሀይሎች አዲስ መርሀ ግብር በመንደፍ በጋራ መታገል ይኖርብናል በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ ስፍራዎች ለተፈጸሙት ግድያዎች ይፋረዳቸዋልም ብሏል።

በተያያዘ ዜና የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብቶች ሊግ በወልዲያ የተፈጸመውን ግድያ በትውልድና በብሔራዊነት ላይ የተቃጣ በማለት አውግዞታል።

ሊጉ በመግለጫው በተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙትን ግድያዎች በማስታወስና በወጣቶች ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ አጥብቆ በመቃወም አሁን ያለው አገዛዝ ወጣቶችን ኢላማው አድርጓል በማለት ውግዘቱን ይቀጥላል።

“በቃ ማለት በቃ ነው” የሚለው የሊጉ መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዝምታ መውጣት አለብት ሲል ጥሪውን ያቀርባል።

በጋራ በመሆን ግድያ ይቁም በማለት የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ካምፑ እንዲመለስ ማድረግ አለበትም ሲል መግለጫውን ያጠቃልላል።