ላለፉት 22 ቀናት በውሃ እጦት የሚሰቃዩት የናዝሬት ከተማ ነዋሪዎች: አሁንም የውሃ አቅርቦታቸው እንዳልተመለሰ ታወቀ:: ከስፍራው ያገኘነው ዜና እንደሚያመለክተው፤ ትላንት እሁድ ውሃ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ቢደረግም እስከ ዛሬ ድረስ ውሃ እንዳልመጣ ታውቋል::
ከአዲስ አበባ 100 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘው የናዝሬት ከተማ፤ 500 ሺህ አካባቢ ነዋሪዎች ያላት፤ ከኢትዮጵያ 2ኛዋ ትልቅ ከተማ ስትሆን፤ ባለፈው ነሐሴ 20 በቆቃ ግድብ ውሃ የሚያስተላልፈው ቧንቧ በጎርፍ ተጠርጎ ከተቋረጠ በኋላ፤ የውሃ አቅርቦት ተቋርጦ የከተማው ውሃና ፍሳሽ በ10 ቦቴዎች ከቆቃ ግድብ ውሃ እያመላለሰ ያቀርብ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል::
የከተማው ነዋሪዎች፤ የከተማው ውሃና ፍሳሽ በቦቴ የሚያከፋፈለውን ጋዝና ዘይት የተደባለቀበት ውሃ ለመጠጣት አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና፤ ከአዲስ አበባና ጎረቤት ከተሞች የሚመጣ ውሃ በ20 ሊትር ጄሪካን እስከ 80 ብር እየተቸበቸበ መሆኑን ዘግበዋል::
ነዋሪዎቹ በወረርሽኝና ውሃ ወለድ በሽታ ልንጠቃ እንችላለን የሚል ስጋት እንደያዛቸውም ሪፖርተር ዘግቧል:: በተያያዘ ዜና፤ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢም ላለፉት 6 ቀናት የውሀ አገልግሎት እንደተቋረጠ ምንጮቻችን ከአዲስ አበባ ዘግበዋል።