የአባይ ግድብ መዋጮ አሁንም ሰራተኛውን እያስመረረ ነው

መስከረም ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የሞግዚት አስተዳደር ሰሞኑን ማንኛውም ሰራተኛ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በድጋሚ የወር ደሞዙን በአመት እንዲከፍል ያወጡት ትእዛዝ የመንግስት ሰራተኛውን እያስመረረ ነው።

የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት የአቶ መለስን ራእይ ለማሳካት በሚል የተጣለው አዲስ የመዋጮ ኮታ ፣ የህዝቡን ስቃይ ማባባሱን ነው ዘጋቢያችን ከባህርዳር የገለጠው።

በሌላ በኩል ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩት ኢንቨስተሮች ለግድቡ ማሰሪያ ቃል የገቡትን 190 ሚሊዮን ብር  በሚቀጥሉት 10 ቀናት አጠናቀው እንዲያቀርቡ አዟል።

የግብር ሚኒስቴር ሰሞኑን በጠራው ስብሰባ ከመስኩ ባለሀብቶች 323 ሚሊዮን ብር  ለመሰብሰብ ቢያቅድም በአመት ውስጥ ለመሰብሰብ የቻለው 64 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ፎርቹን ዘግቧል። ባለሀብቶች ቃል የገቡትን ገንዘብ ለመክፈል ያልቻሉት በግብርናው ዘርፍ ላይ በታየው የገበያ ችግር ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ጊዜ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች 189 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ቢገቡም፣ እስካሁን ድረስ የለገሱት ግን 20 ሚሊዮን ብር ገደማ ብቻ መሆኑን ፎርቹን ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተያዘው የበጀት ግማሽ አመት ውስጥ ወደ 1 ቢሊዮን ብር  የሚጠጋ የቦንድ ሽያጭ ፈጽሟል።

አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት በአባይ ላይ የሚያደርገውን ግንባታ እንዲያቆም መጠየቁ ይታወሳል። ለግድቡ መስሪያ ከሚያስፈልገው ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ውስጥ እስከዛሬ ከህዝብ የተሰበሰበው ከ8 ቢሊዮን ብር እንደማይበልጥ ታወቋል። አቶ መለስ ዜናዊ የአረቡን አለም አመጽ ተከትሎ ፣ በአገሪቱ ተመሳሳይ አመጽ እንዳይነሳ የህዝቡን ትኩረት ለማስለወጥ  የአባይን ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸውን በወቅቱ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጅ አቶ መለስ ይህን አለም ከተሰናበቱ በሁዋላ ፣  የአባይ ፕሮጀክት ለአቶ ሀይለማርያም መንግስት ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ  እንደሚቀጥል ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚናገሩት።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide