ቴዲ አፍሮ በግዮን ሆቴል የተሳካ ኮንዘርት አካሄደ

ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዕውቁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቅዳሜ ምሽት በግዮን ሆቴል ያዘጋጀው <ኮንሰርት> እጅግ የተሳካ እንደነበር በስፍራው የተገኙት የኢሳት ሪፖርተሮች ዘግበዋል።

ኮንሰርቱ በነበረው ድምቀት እስከዛሬ ከተደረጉት የሙዚቃ ኮንሰርቶች  ሁሉ  በቀዳሚነት ስፍራ የሚመደብ ነው ያሉት ዘጋቢዎቻችን፤ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁንም አቡጊዳ ከሚለው የመጀመሪያው አልበሙ ጀምሮ እስከ አዲሱ <ጥቁር ሰው> አልበም ድረስ ከተካተቱት ሙዚቃዎቹ ጥቂት የማይባሉትን በጥሩ ትንፋሽና በብቃት ተጫውቷቸዋል ብለዋል።

አርቲስቱ ከዚህም ባሻገር መድረኩን በመቆጣጠር ረገድ ልዩ ብቃቱን ያሳየበት ምሽት እንደነበርም፤ ዘጋቢዎቻችን አመልክተዋል።

በተለይም  ቴዎድሮስ <ጃ ያስተሰርያል> የሚለውን ዘፈኑን ሲጫዎት ታዳሚው ህዝብ በልዩ ስሜት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አብሮት መዝፈኑን   የኢሳት ዘጋቢዎች አመልክተዋል።

ዘፈኑ እንዳለቀም ህዝቡ በአንድ ድምፅ፦< ይደገም!ይደገም!> በማለት ዘፈኑ እንዲደገምላቸው መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም አርቲስት ቴዲ አፍሮ  ዘፈኑን እንደማይደግመው በመጥቀስ፤ የዘፈኑ ዋነኛ መልዕክት  ነው ያላትንና ፦<አዲስ ንጉስ እንጂ፤ለውጥ መቼ መጣ?> የምትለውን  ስንኝ በቃሉ በመድገምና የፍቅርን ሀይልነትና አሸናፊነት በመስበክ ወደ ቀጣዩ ሙዚቃው ተሻግሯል ።

በዘፈኑ የታየው የታዳሚው ስሜት፤  የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት  አሁንም እየተቀጣጠለ እንደሚገኝ የሚያመላክት መሆኑን፤ ኮንሰርቱን የተከታተሉ ሁሉ ይስማማሉ።

ቴዲ ከእስር ተፈትቶ በውጪ አገር የሚዚቃ ስራዎቹን ሊያቀርብ በመጣ ጊዜ <ጃህ ያስተሰርያል> የሚለውን ሙዚቃውን   ሳይጫወተው መቅረቱ፤ አንዳንድ አድናቂዎቹን ቅር ማሰኘቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ቅር የተሰኙት አድናቂዎቹ  ቴዲ ሙዚቃውን አለመጫዎቱን፤ ዘፈኑ ካለው ፖለቲካዊ መልዕክት አኳያ ከፍርሀት ጋር ሲያይዙት የነበረ ቢሆንም፤ወጣቱ ብላቴና  ግን ሙዚቃውን እዚያው አገር ቤት በማቀንቀን ለተነሳበት ቅሬታ ተግባራዊ ምላሹን ሰጥቷል።

ቴዲ አፍሮ በመቀጠልም በአዋሳ ተመሣሳይ <ኮንሰርት> ሚያዘጋጅ ሲሆን፤ አዋሳዎች ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ እንደሚገኙ በስፍራው ያለው ወኪላችን በስልክ ገልጾልናል።

ለረዥም ጊዜ ተቀዛቅዞ የቆየው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ገበያ የቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው አልበም መውጣቱን ተከትሎ ነፍስ እንደዘራ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ።