በሀረር ከፍተኛ የሆነ የውሀ እጥረት ተከስቷል

ጥቅምት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከአካባቢው ህዝብ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የከተማውን የውሀ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከሶስት ወራት በፊት አዲስ የውሀ ፕሮጀክት ቢመረቅም የከተማው የውሀ ችግር አሁንም ተባብሶ ቀጥሎአል። ነዋሪዎች እንደሚሉት 20 ሊትር ውሀ ከአምስት እስከ 10 ብር እየተሸጠ ነው።2 ሊትር የሚይዙ የውሀ ላስቲኮች በ14 ብር እየተሸጡ  ነው።  ውሀው ከሩቅ ቦታ የሚመጣ በመሆኑም ህዝቡ በፈለገው ጊዜ ለማግኘት አልቻለም።

ላለፉት 10 ቀናት የተቋረጠው መብራት ተመልሶ ቢመጣም ህዝቡ ግን መብራቱን ወስደው ውሀውን ይመልሱን እያለ መሆኑን አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ነዋሪ ለኢሳት ተናግሯል።  በአካባቢው ያለው የውሀ ችግር በቶሎ የማይቀረፍ ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ችግር ሊከሰት እንደሚችል፣ ምናልባትም ህዝባዊ ተቃውሞ ሊያስነሳ እንደሚችል ነዋሪው ተናግሯል።

በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢውን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡