ታዋቂ አፍሪካውያን ወደ ውጭ ተዘርፎ በሚወጣው ገንዘብ ላይ የቡድን 8 እና 20 አገራት እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ማድረግ ጀመሩ

ግንቦት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ለኢሳት በላከው መረጃ የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን፣ የታዋቂው የነጻነት አባት የኔልሰን ማንዴላ ባለቤት ግራሺያ ሚሼል እና ሌሎች ታዋቂ አፍሪካውያን በጋራ ለቡድን 8 እና ለቡድን 20 አገራት መሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ከአፍሪካ ባለፉት 9 አመታት ተዘርፎ በውጭ ባንኮች የተቀመጠው 385 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ አህጉሪቱ እንደሚለስ ጠይቀዋል።

ኮፊ አናንና ሌሎች ታዋቂ አፍሪካውያን በጋራ ባጠኑት ጥናት ከዚህ ቀደም በግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ የተጠናውን ጥናት ትክክለኛነት ያረገጋጠ መሆኑን ድርጅቱ በላከው መረጃ አመልክቷል።

ኮፊ አናን ለቡድን 8 አገራት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ሚስጢሩ እንዲገለጽ፣ ዝምታው እንዲሰበር ጠይቀዋል።

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ እኤአ ከ2000 እስከ 2009 ባሉት 8 አመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ 11 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ተዘርፎ መውጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ከ2010 እስከ 2011 ባሉት አመታት  ደግሞ በእያመቱ ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ተዘርፎ በውጭ ባንኮች መቀመጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ ከ2000 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ የወጣው ገንዘብ ከኢትዮጵያ አመታዊ በጀት ጋር እኩል ነው።

ኮፊ አናን እና ታዋቂ አፍሪካውያን ባወጡት ሪፖርት ለአፍሪካ በእርዳታ ስም የሚሰጠው ገንዘብ ከአፍሪካ በተለያዩ መንገዶች ተዘርፎ ከሚወጣው ገንዘብ ያላነሰ ነው። በተመሳሳይ መንገድም ኢትዮጵያ በእያመቱ በህገወጥ ዝርፊያ የምታጣው ገንዘብ አገሪቱ በእርዳታ ከምታገኘው ገንዘብ ጋር ተመሳሳይ መጠን አለው።

ታዋቂ አፍሪካውያን ይህን ገንዘብ ለማስመለስ የሚያደርጉት ጥረት መሳካቱ ለወደፊቱ የሚታይ ቢሆንም፣ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቱ በላከው መረጃ ላይ እንዳመለከተው አብዛኞቹ የተዘረፉ ገንዘቦች የሚገኙት በአሜሪካ፣ እንግሊዝና ስዊዘርላንድ መሆኑን በመጥቀስ፣ የእንግሊዙ መሪ ዴቪድ ካሜሩን የቡድን 8 አገራት ግፊት ማድረግ መጀመራቸውን ገልጿል።

በሌላ ዜና ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ሚዛን ጉድለት እየሰፋ መምጣቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ጋዜጣው ብሄራዊ ባንክን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ባለፉት 9 ወራት ወደ ውጭ  ምርት በመላክ ያገኘቸው ገቢ 2 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ዶላር ወይም ወደ 40 ቢሊዮን ብር አካባቢ ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸው የ8 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ165 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ምርት በመሆኑ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ 6 ቢሊዮን 600 ሚሊዮን ወይም ከ125 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

ዲያስፖራው ወደ አገሩ የሚልከው ገንዘብ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ እየሆነ መምጣቱም ተመልክቷል።