ባህርዳር የተፈጸመው ግድያ እንቆቅልሽ እስካሁን አልተፈታም

ግንቦት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በባህርዳር 17 ሰዎችን በጥይት አርከፍክፎ በግፍ ከገደለው የፌደራል ፖሊስ አባል ፈቃዱ ናሻ ጋር በተያያዘ ግድያው ሲፈጸም በዝምታ ተመልክታችሁዋል በሚል 10 የፊድራል ፖሊስ አባላት ታሰረዋል፡፡  የገዳዩ የቀድሞ ፍቅረኛም ድርጊቱ ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ በህግ ቁጥጥር ስር እንደምትገኝ ታውቋል፡፡

የፊደራል ፖሊስ ዋና  አዛዥ ጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ ትላንት የተጎጅ ቤተሰቦችን ጎብኝተዋል፡፡

የተጎጅ ቤተሰቦች ለጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ “ገዳዩ ወታደር  የተቀበረበት ቦታ ይታወቅልን አለበለዚያ ለኦሮሚያ ክልል ተላልፎ ከተሰጠ አማራን የገደለ እየተባለ ግለሰቡ እንዲመለክ ይሆናል” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል ። ገዳዩ የተቀበረበት ቦታ መንግስት  ይፋ ለማድረግ አልፈለገም።

የአካባቢው ነዋሪዎች ግድያውን በመቃወም የተቃውሞ  ሰልፍ ለማድርግ ወደ አደባባይ ለመውጣት ሙከራ ቢያደርጉም መንግስት ፈቃድ ከልክሎቸዋል፡፡ በአካባቢው የነበሩ የፊድራል ፖሊሶችም በሙሉ በልዩ ሃይሎች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ በቁጥጥር ስር የዋሉት የፌደራል ፖሊስ አባላት የህዝቡን ስሜት ለማረጋጋት ተብሎ ይታሰሩ  ወይስ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል ባለመቻላቸው የታወቀ ነገር የለም።

የክልሉ የፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ወርቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ገዳዩን ወታደር ለመያዝ ሙከራ ሲያደርጉ ውሀ ውስጥ በመግባት ራሱን ማጥፋቱን ለኢሳት መናገራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጅ በቂ እርምጃ አልወሰዳችሁም በሚል 10 የፌደራል ፖሊስ አባላት መታሰራቸው ኮሚሽነሩ የሰጡትን መግለጫ ለመቀበል አዳጋች እንዳደረገውና  ግድያው ውስብስብ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑን እንደሚያመለክት ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የክልሉ ባለስልጣን ተናግረዋል። በአካባቢው ያሉትን የፌደራል ፖሊሶች በማስወጣት በልዩ ሀይሎች ለመተካት ለምን እንደተፈለገም ግልጽ አይደለም።

ከ17 ያላነሱ ሰዎችን በግፍ የገደለው የፌደራል ፖሊስ አባል አሟሟትና መንግስት ዘገባውን ያቀረበበት መንገድ ህብረተሰቡን ለከፍተኛ ጥርጣሬ መዳረጉን መዘገባችን ይታወሳል። የክልሉ ነዋሪዎች በመንግስት በኩል የቀረበውን ዘገባ እስካሁን አልተቀበሉትም።

በጉዳዩ ዙሪያ  አስተያየታቸውን የጠይቅናቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት  ሃላፊ የሆኑት ምክትል ኮማንደር ዋለልኝ ዛሬ ስላልተዘጋጀሁ መልስ ለመስጠት አልችልም በሌላ ጊዜ  ደውልልኝ ብለዋል።