ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ካርዲናል ሆኑ

ታኀሳስ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳትና የኢትዮጵያ ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል የካርዲናልነት ማዕረግ አገኙ፡፡

ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስን ጨምሮ ለ15 ሊቃነ ጳጳሳት የካርዲናልነት ማዕረግና ለአምስት ሊቀ ጳጳሳትና ጳጳሳት ደግሞ ድምፅ አልባ  የካርዲናልነት ሹመት ባለፈው እሑድ ረፋድ ላይ በቫቲካን በመስጠት ይፋ ያደረጉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ናቸው፡፡

ቫቲካን ሬዲዮ ታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዳስታወቀው፣ የአዲሶቹ 15 ካርዲናሎች በዓለ ሲመት በቫቲካን የሚፈጸመው የካቲት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡

20ዎቹ ተሿሚዎች ከሁሉም ክፍለ ዓለም ከሚገኙ ከ14 አገሮች የተውጣጡ ሲሆን፣ ስብጥሩም የሮም ካቶሊካዊ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ካሉት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ትስስር የሚገልጽ መሆኑን አቡነ ፍራንሲስ አስታውቀዋል፡፡

ሁለተኛው አፍሪካዊ ካርዲናል የሆኑት የኬፕቨርዴው ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፣ ከተመረጡት አምስቱ አረጋውያን ጳጳሳት መካከል ደግሞ የሞዛምቢኩ ጳጳስ ይገኙበታል፡፡

የአቡነ ብርሃነየሱስ ካርዲናል መሆንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ደስታዋን ገልጻለች። የቤተ ክርስቲያኒቷ ሊቀ ጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ አባ ተስፋዬ ወልደማርያም ለቫቲካን ሬዲዮ እንደተናገሩት፣ የካርዲናልነት ሹመቱ ለአገሪቱ ትልቅ ክብርና ኩራት ነው

ሊቀ ጳጳሳቱ ለካርዲናልነት ሹመት የበቁት ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ባደረጉት ከፍተኛ መንፈሳዊና ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ዕድገት አስተዋጽኦ መሆኑ ተናግሯል፡፡

ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ደምረው ሱራፌል፤ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፣ የተወለዱት ሐምሌ 7 ቀን 1940 ዓ.ም. በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ከሐረር ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ጨለቅለቃ ነው፡፡

የነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) እና የፍልስፍና ትምህርታቸውን በአገር ውስጥና በእንግሊዝ ሲያጠናቅቁ፣ ከኢጣሊያ ግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲም በሶሲዮሎጂ የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡