ምርጫ ቦርድ ፤አንድነትና መኢአድ በምርጫው ላይሳተፉ ይችላሉ አለ።

ታኀሳስ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አንድነት፤ ከምርጫው ከታገድኩ  ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው የሚሆነው አለ።

አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት)እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)  የውስጥ ችግሮቻቸውን ካለፈቱ የምርጫውን ሂደት ላይሳተፉ ይችላሉ ሲል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስጠነቀቀ።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ  ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር ፦ሁለቱ ፓርቲዎች በውስጥ  ህገ ደንባቸው ሊሄዱ እንዳልቻሉ በመጥቀስ፤ ይህንንም አስመልክቶ ቦርዱ  ሊያወያያቸው ቢሞክርም ሊግባቡ አልቻሉም ብለዋል። በመሆኑም ቦርዱ በጉዳዩ ላይ በመጪው ማክሰኞ ውይይት እንደሚያደርግ ምክትል ሰብሳቢው ለድርጅት ብዙሀን መገናኛዎች ተናግረዋል።

ችግርን ለመፍታት እና ለህግ ተገዢ የመሆን ቁልፉ በፓርቲዎቹ እጅ ይገኛል ያሉት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ፤ ፓርቲዎቹ ለህግ ተገዢ ሆነው በምርጫ የመወዳደር ዕድሉ አሁንም እንዳላቸውም ገልጸዋል። በፓርቲዎቹ የታዩ ችግሮችን በተመለከተ ቀደም ሲል  በተደጋጋሚ መግለጫ ተሰጥቷል ያሉት  ዶክተር አዲሱ፥ ችግሮቻቸውን በመተዳደሪያ ደንባቸው መሰረት መፍታት ካለቻሉ  በመጪው ግንቦት የሚካሄደው ምርጫ ላይ እንደማይሳተፉ  ተናግረዋል።

ኢሳት ከሁለት ሳምንት በፊት ስለፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ምዝገባ ባስተላለፈው ዜና አንድነትና መኢአድ ከምርጫ ቦርድ ጋር በተፈጠረ ውዝግብ በምርጫው የመሳተፋቸው ነገር አጠራጣሪ  እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር አቶ አስራት አብርሀ  በሰጡት ምላሽ ፤ቦርዱ የሚሰበሰበው ገና ዛሬ ሆና ሳለ ፤ምክትል ሰብሳቢው ከአንድ ቀን በፊት በድርጅት ሚዲያ መግለጫ መስጠታቸው  ስህተትና በቦርዱ ውሳኔ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥር መሆኑን በመጥቀስ፤አንድነት መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በሙሉ ማድረጉንና ያልፈታው ችግር እንደሌለ ገልጸዋል።

ቦርዱ አንድነት በምርጫው እንዳይሳተፍ ከወሰነ ፤ ሆን ተብሎ አንድነት በምርጫው እንዳይሳተፍ የማድረግ  ፖለቲካዊ ነው የሚሆነው ያሉት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አስራት አብርሐ ፤ያኔ አንድነትም  ለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ የራሱን ፖለቲካዊ ውሳኔ ይወስናል ብለዋል። ወደ ምርጫው ስንገባ እናሸንፋለን፤አናሸንፍም በሚል ስሌት ሳይሆን ህዝቡን በዚህ መልክ በማንቃት ለተሻለ ትግል የምናደራጀበትን መንገድ እንከፍታለን ብለን ነው ያሉት አቶ አስራት፤ “ቦርዱ እንዳንሳተፍ ከከለከለን ምንም የሚያደናገጠን ነገር የለም፤እንደውም ቀጥታ ህዝቡን ወደማደራጀትና ወደማታገል እንድንገባ መንገዱን ነው የሚያቀልልን      ” ብለዋል።