ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሊባኖስ ቤይሩት ከ60-80ሺህ የሚገመቱ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ ተባለ፣ ከነዚህ ዉስጥ ህጋዊ የሆኑት 43ሺህ ብቻ ናቸዉ
በብሪታኒያ የሚታተመዉ ጋርዲያን ጋዜጣ ይህን የገለፀዉ በቅርቡ በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንሱላ ደጃፍ ላይ በአስቀጣሪዋ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድባ ወደ አዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ከተወሰደች በሁዋላ እራሷን ሰቅላ አጥፍታለች ስለተባለችዉ የሁለት ልጆች እናት ዓለም ደቻሳ ባወጣዉ ዘገባ ላይ ነዉ።
የጋዜጣዉ ዝግጅት ክፍል በኢትዮጵያ ቡራዩ በሚገኘዉ የመኖሪያ ቤቷ በመገኘት ቤተሰቦቿን፤ ባለቤቷ አቶ ለሜሳ እጄታን፤ ተስፋዬና የአብስራ የተሰኙትን የ12 አመት ወንድ ልጇንና የ4 አመት ሴት ልጇን እንዲሁም ሌሎች የቅርብ ዘመዶቿን ከተመለከተና ካነጋገረ በሁዋላ ባቀረበዉ ሰፊ ሀተታ ነዉ።
የጋዜጣዉ ሪፖርተር በአካባቢዉ ስለተመለከተዉ የኑሮ ሁኔታ… “አለም ወደ ብቸኝነት ሞቷ ያደረገችዉን ጉዞ በጀመረችበት ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘዉ ቡራዩ ከተማ እንደ አለም ያሉ እናቶችና እንደ ባለቤቷ ያሉ አባቶች እያንዳንዱን ቀን ከሞት ተርፎ ለማደር እንደጥንታዊዉ ግሪካዊ ሄርኩለስ እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የስቃይ ህይወት በመምራት ላይ እንዳሉ ገልጿል።
የ33 አመቷ የልጆች እናት የኢትዮጵያ መንግሰት ወደ ሊባኖስ የሚደረገዉን ጉዞ ቢያግድም ለልጆቻቸዉ የተሻለ ሕይወት በተስፋ ከሚጓዙት ዉስጥ አለም አንዷ መሆኗን በመጥቀስ ዉሳኔዉ ልብ የሚሰብር ነዉ በማለት ገልጾታል። ከአለም ጋር ለመጓዝ እቅድ የነበራት ታደሉ ነጋሽ የተባለች ጎረቤቷ በበኩሏ “ ሌላ ምርጫ የለንም፡ ልጆቻችን እንደእኛ እንዲሰቃዩ አንፈልግልም። በአለም ላይ የደረሰዉን ስናስብ በጣም እናዝናለን፡ ነገር ግን እዉነቱን እዚህ ስታይ ችግሩ በላይ በላዩ ነዉ፤ በጣም የሚያሰቃይ፤ እናም ይሄን ያህል መጥፎ ሃሳብ አይደለም።” ብላለች።
በአለም ደቻሳ ላይ የተፈፀመዉን ኢሰብኣዊ ድርጊት በተመለከተ የአለም አቀፉ የሰብኣዊ ምብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛዉ ምስራቅና የሰሜን አፍሪቃ ምክትል ዳይሬክተር ናዲም ሁሪ የሊባኖስ መንግስት በሚከተለዉ ጥብቅ የቪዛ ደንብ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግና የሰራተኛ ህግ ለቤት ሰራተኞችም ሊዉል እንዲችል እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በሊባኖስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባደረጉት ጥናት መንግስታቸዉ አለምአቀፍ የሰብኣዊና የሲቪል መብቶች የሚጠይቀዉን ደንብ ለማሟላት በ3 ጉዳዮች ዙርያ፤ በቤት ሰራተኛነት ተቀጥረዉ ከተለያዩ አገሮች በሚመጡ የዉጭ አገር ሴቶች ፤ የህብረተሰቡ ግማሽ ሃይል በሆኑትና በደል በሚደርስባቸዉ የሊባኖስ ሴቶች ፤ እንዲሁም በፍልስጤማዉያን የመስራትና የቤት ባለቤት በመሆን መሰረታዊ የሲቪል መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና ተግባራዊ እንዲያደርግ ማሳሰባቸዉን ካዉንተር ፐንች Counterpunch የተባለዉ የመረጃ ምንጭ ገልጿል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide