የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በገዳሪፍ ጥቃት ይቅርታ ጠየቀ

ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት በገዳሪፍ አስተዳዳሪ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ይቅርታ ጠየቀ
በአርማጭሆ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥቃቱን የፈጸሙት የገዳሪፍ አስተዳዳሪ የሆኑት ካርም አል አባስ ከአማራ ክልል ፐሬዚዳንት አያሌው ጎበዜ ጋር ለመነጋገር ወደ አካባቢው ሲያመሩ ነው። ኢሳት በትናንት ዜናው ጥቃት የተፈጸመባቸው የካርቱም አስተዳዳሪ መሆናቸውን ቢዘግብም ፣ ሱዳን ትሪቢዩን ዛሬ ይዞት በወጣው ዘገባ ግን አስተዳዳሪው የካርቱም ሳይሆን የገዳሪፍ ናቸው ብሎአል።
አል አባስ ጥቃት የተፈጸመባቸው ኡም ዳባሎ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። አንድ የኢትዮጵያ ገበሬ እርሻ ሲያርስ መመልከታቸውን ተከትሎ አስተዳዳሪው ከገበሬው ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። አስተዳዳሪው ገበሬው የሚያርሰው መሬት የሱዳን መሆኑን እየነገሩት ባለበት ሰአት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በእርሳቸውና በአጃቢዎቻቸው ላይ ተኩስ ከፍተውባቸዋል። ሚስተር አባስም ጉዞዋቸውን በመሰረዝ ተጨማሪ ሀይል እንደሚጣላቻው ማድረጋቸውን ፣ ሱዳን ከደረሱ በሁዋላም ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ኢሳት ትናንት ባቀረበው ዘገባ 5 የአስተዳዳሪው አጃቢዎች መቁሰላቸውን መግለጡ ይታወሳል ። አስተዳዳሪው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን ሚሊሺያዎች ለማደን ዘመቻ እንደሚጀምሩ፣ የአካባቢውን ጎሳዎች በማስታጠቅ ታጣቂዎችን እንዲወጉ እንደሚያደርጉ ዝተዋል።
የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አያሌው ጎበዜ ለተፈጸመው ድርጊት ይቅርታ መጠየቃቸው እና ጥቃት ፈጻሚዎች ለማደን ቃል መግባታቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል። የገዳሪፍ የጸጥታ ሀይሎች ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ 12 ኢትዮጵያውያንን ይዘው አስረዋል።
የመለስ መንግስት ከ5 አመት በፊት እጅግ ሰፊ የሆነ መሬት ለሱዳን ቢሰጥም፣ በጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውአን ግን የመንግስትን ውሳኔ አልተቀበሉትም። በዚህም የተነሳ አሁንም ለሱዳን በተሰጠው መሬት ላይ የእርሻ ስራ እያከናወኑ ነው። አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን እንደማይሰጡ፣ የሱዳን መንግስት በሀይል ለማስመለስ ቢሞክር የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስዱ እየዛቱ ነው። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወገኖች እንዳሉት በአስተዳዳሪው ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመ በሁዋላ በርካታ ገበሬዎች እየተዋከቡ ነው። የገዳሪፍ ባለስልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተው በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያሰሩ ባለበት ሰአት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የሆነው አያሌው ጎበዜ ማበረታቻ መስጠቱ እንዳበሳጫቸው ገልጠዋል። በጠርፍ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የሱዳን መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቶ ሰዎችን እየወሰደ ማሰሩን እንዲያቆም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሚመለከተው ሁሉ አቤት እንዲሉ ጠይቀዋል።
__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide