200 የሚሆኑ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሰራተኞችን ከስራ ሊያሰናብት ነው

ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢህአዴግ 200 የሚሆኑ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ሰራተኞችን ከስራ ሊያሰናብት መሆኑ ታወቀ
ቢ ፒ አር እየተባለ በሚጠራዉ የመንግስት የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የግምገማ ዉጤት መሰረት እንዲሰናበቱ የተወሰነባቸዉ ሰራተኞች በጥበቃ፤ በጥገናና በፅዳት ሙያ ለረዢም አመታት ሲያገለግሉ ከነበሩ የኤጀንሲዉ ሰራተኞች መካከል እንደሆኑ ተገልጿል። ከመካከላቸዉ የ15 አመት የስራ አገልግሎት ዘመን ያሏቸዉና አብዛኛዎቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸዉ።
የአንድ አመት ደመወዛቸዉ ተከፍሏቸዉ እንዲሰናበቱ የተፈረደባቸዉ ሰራተኞች ዉሳኔዉን እንዳልተቀበሉትና አቤቱታቸዉን ለከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ማቅረባቸዉ ቢታወቅም የኤጀንሲዉ ባለስልጣኖች በተገኙበት ከሚኒስቴሩ መ/ቤት የጡረታ መብታቸዉ የሚጠበቅላቸዉ እድሜያቸዉ ሲደርስ ጡረታቸዉን ሊያገኙ እንደሚችሉ፤ በአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተዉ ለመስራት ፈቃደኛ ለሚሆኑት ኤጀንሲዉ ስልጠና ሊሰጣቸዉ እንደሚችልና ከዚህ ዉጭ ስንብቱን የሚቃወሙ በጀመሩት አቤቱታ እንዲገፉበት የተፈቀደላቸዉ መሆኑ ተገልፆላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአነስተኛ ኢንዱስትሪ ለሚደራጁት ለስራ የሚሆኗቸዉ ቤቶች እንደሚሰጣቸዉና አንዳንድ የኮንትራት ስራዎችን ከኤጀንሲዉ መዉሰድ እንደሚችሉ የተገለጸላቸዉ ሲሆን ሰራተኞቹ የተሰጧቸዉን የተስፋ ቃሎች እንዳልተቀበሏቸዉ ለማወቅ ተችሏል።
__________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide