በጨለንቆ በትንሹ ስድስት ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010)

በሀረርጌ ጨለንቆ ዛሬ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በትንሹ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ታወቀ።

በኢትዮጵያ ሶማሌ እና ኦሮምያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢም በተነሳ ግጭት ከ7 ያላነሱ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ14 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው መረጃ አድርሰውናል።
ለተቃውሞ መነሻ የሆነው ደግሞ ላለፉት ተከታታይ ወራት ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ሲፈጽም የቆየው የሶማሌ ልዩ ሃይል በአንድ የኦሮሞ ተወላጅ ላይ ግድያ በመፈጸሙ ነው።

የልዩ ሃይሉ ርምጃ ያስቆጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተቃውሞ በሚያሰሙበት ሰዓት ከሃረር ከተማ የተነሱ ወታደሮች ወደ አካባቢው በመሄድ በህዝቡ ላይ በከፈቱት ተኩስ 6 ሰዎችን ገድለው 14ቱን ያህል ሰዎችን ማቁሰላቸው ታውቋል።

ከቆሰሉት መካከል 6ቱ ክፉኛ በመጎዳታቸው ወደ ድሬዳዋ ሆስፒታል ተወስደዋል።
የሶማሌ ልዩ ሃይል አባላት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመተባበር በህዝቡ ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ሊቆም አለመቻሉን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።

የመከላከያ አባላት ገለልተኛ በመሆን የሶማሌ ልዩ ሃይልን ጥቃት ያስቆማል የሚል ግምት ተቀምጦ ነበር።

ነገር ግን መረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ከሆነ በአካባቢው የሚታየው ሁኔታ ሁለቱ ሃይሎች ጥምረት ፈጥረው በህዝብ ላይ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን ነው።
የአሁኑ ጥቃት የተፈጸመው የብሄር ብሄረሰቦች በአል በተከበረ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑም ታውቋል።

በበአሉ ላይ ሀገሪቱ የብሄር ፈዴራሊዝምን ከገነባች በኋላ የብሄር ግጭቶችን ማስወገድ መቻሏን የአገዛዙ ባለስልጣናት ሲናገሩ ተሰምተዋል።

እነሱ ይህን ይበሉ እንጂ በአሉ እየተከበረ በሚገኝበት ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለስልጣናት የሚቆሰቁሷቸው የብሄር ግጭቶች ሲካሄዱ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምን ያህል ሰዎች እስካሁን እንደተያዙ ባይታወቅም በሱሉልታ ታጣቂዎች ቤት ለቤት በመሄድ አፈሳ መጀመራቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ኢሳት ምን ያህል ሰዎች በታጣቂዎቹ እንደተያዙ ለማጣራት ሙከራ በማድረግ ላይ ነው።