በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010)

በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ።

በግቢው ውስጥ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱም ተሰምቷል።–የቅስቀሳ ወረቀት በመበተን ላይ መሆኑም ታውቋል።

በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን ተከትሎ በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ግጭት ተቀስቅሷል።

በወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተነሳ ግጭት በትንሹ 4ተማሪዎች ተገድለዋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የህወሃት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቅ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።

በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የሚደረሰውን ጥቃት በመቃወም ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ላይ ውጥረት መንገሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በደብረታቦር ዩንቨርስቲ የተነሳው የተማሪዎች ተቃውሞ መባባሱን ማምሻውን የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

በዩኒቨርስቲው ባለፈው ሳምንት የተከበረውን የብሄረሰቦች ቀን ተከትሎ በአጋዚ ወታደሮች ድብደባ መፈጸሙን የሚገልጹት ተማሪዎች የተቃውሞ የጥሪ ወረቀት መበተኑንና በዚህም ተቃውሞ መነሳቱን ይጠቅሳሉ።

ዛሬ ምሽቱን ተማሪዎቹ ተቃውሞውን ያነሱ ሲሆን በከተማዋ የሰፈረው የአጋዚ ሰራዊት ተማሪዎቹን ለማፈን እየተሯሯጠ እንደሆነም ታውቋል።

ተቃውሞውን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ የእሳት ቃጠሎ ተነስቷል። ከደብረታቦር ወደ ጋይንት ጋሸና መስመር የሚወስደው መንገድ በአጋዚ ታጣቂዎች መዘጋቱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአዲግራት ባለፈው ዓርብ የተነሳው ግጭት ብሄርን መነሻ ያደረገ በመሆኑ በአማራና ኦሮሞ ተወላጅ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ላይ ጉዳት አስከትሏል።

ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ የገባው የአጋዚ ሃይል የሁለቱን ብሄረሰብ ተወላጆችን እየመረጠ መደብደቡን የገለጹት ተማሪዎች ለጊዜው ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል። ቁጥሩ ከዚያም ሊልቅ እንደሚችል ይነገራል።

የአዲግራቱን ጥቃት ተከትሎም በመላው የአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በወልዲያ ለአራት ተማሪዎች ሞት ምክንያት የሆነ ግጭት ተከስቷል።

በባለፈው ሳምንት ግጭት የወልዲያን ዩኒቨርስቲ የከበቡትና ለትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩት የአጋዚ ወታደሮች ዛሬ በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ በመዝለቅ ተማሪዎችን መደብደባቸው የተገለጸ ሲሆን በርካታ ተማሪዎች ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው ታውቋል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በጠዳ ካምፓስ የተጀመረው ተቃውሞ ሰፍቶ በሶስቱም ካምፓሶች መቀጠሉ የታወቀ ሲሆን የህወሃት አገዛዝ ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ መፈክሮች በስፋት መሰማታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በጎንደሩ ተቃውሞ ቀድመው ከግቢው እንዲወጡ የተደረጉትና በታጣቂዎች ጥበቃ የሚደረግላቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በሆቴል አልጋ ተይዞላቸው እንደሚገኙ የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ግቢውን ለቆ የወጣው ሌላው የዩኒቨርስቲው ተማሪ ግን በአብያተ ክርስቲያናትና በከተማው ነዋሪ ዘንድ ተጠግቶ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜና በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ማምሻውን በተማሪዎች ማደሪያ ቤቶች ከፍተኛ ጩህት እየተሰማ ነው።

አጋዚ ጦር ወደ ግቢው ገብቶ ተማሪዎችን እየደበደ ሳይሆን እንደማይቀር እየተገለጸ ነው።

በወልዲያ ስታዲየም ልዩ ጥበቃ እየተደረገላቸው ቀኑን ያሳለፉት የትግራይ ተወላጅ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ምሽቱንም በጥበቃ ስር ሆነው በዩኒቨርስቲው አዳራሽ ወንበሮች ተገጣጥመው እንዲተኙ  መደረጋቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በአዲግራት ዩኒቨርስቲ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ዛሬም ጥቃት እየደረሰ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ 4ቱም ካምፓሶች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የአጋዚ ጦር  መሰማራቱንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።