ሳውዲ ሲኒማ ቤቶች እንዲከፈቱ ፈቀደች

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010)

ሳውዲ አረቢያ ከ35 አመታት እገዳ በኋላ ሲኒማ ቤቶች በሀገሪቱ እንዲከፈቱ ፈቀደች።

የሀገሪቱ ባህልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሲኒማ ለመክፈት የሚያስችል ፍቃድ ዛሬ መስጠት ጀምሯል።

ባለፈው ሰኔ አልጋ ወራሽነቱን የተቆናጠጡት መሐመድ ቢን ሳልማን በሳውዲ የተለያዩ ለውጦችን ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ አሁን ሲኒማ እንዲታይ መፈቀዱ የዚሁ የለውጥ እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ ተወስዷል።

ራዕይ 2030 በመባል የሚታወቀውና በግዛቲቱ የተለያዩ ለውጦችን ለማድረግ በመንግስት የተያዘው የለውጥ ፕሮግራም በአዲሱ አልጋ ወራሽ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

የሀገሪቱ የባህል ሚኒስትር አዋድ ቢን ሳለህ አል-አዋድ እንደሚሉት በፊልም ቤቶቹ የሚተላለፉት ፊልሞች ይዘት ግን በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ መሰረት ቅድመ ምርመራ ይደረግባቸዋል።

አንዳንድ ተቺዎች ግን ሲኒማ መፈቀዱ አዲስ የነጻነት ርምጃ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ።

ጆሴፍ ፋሂም የተባለ ግብጻዊ የሲኒማ ተቺ ሲናገር የፊልም ባለሙያዎች የንጉሳውያኑን ቤተሰቦችን በተመለከተ ምንም ማለት እንዳይችሉ የሚያደርግ ጠንከር ያለ ሕግ እንዳለ ይገልጻል።

ስለዚህም ይላል ጆሴፍ የሲኒማ ፈቃድ መሰጠቱ እንደ አዲስ የነጻነት ርምጃ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።

የሀገሪቱ የባህልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር በበኩሉ የፊልም ኢንደስትሪው 24 ቢሊየን ዶላርና 30ሺ ቋሚ ስራ በ2030 ይፈጥራል ይላል።

በሚሊየን የሚቆጠሩ በአረብ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ቴክኖሎጂ ባመጣው ለውጥ ምክንያት በኢንተርኔት በሚለቀቁና እንደ ኔት ፍሊክስ ባሉ አገልግሎቶች ፊልም ይመለከታሉ።

ስለዚህ ሳውዳረቢያ ለሲኒማ ቤቶች ፈቃድ መስጠቷ ብዙም ለውጥ አያመጣም ያላሉ ጄን ኪኒሞት የተባሉ በእንግሊዝ የሚኖሩ ተመራማሪ ለአልጀዚራ ሲናገሩ።

አክለውም ሲናገሩ የሳውዲ ዜጎች አሁንም ፊልም ያያሉ ልዩነቱ በብዛት ወደ ሲኒማ ገብተው ማየታቸው ነው ብለዋል።

ለውጥ አራማጅ ተደርገው የሚወሰዱት አልጋ ወራሽ ቢን ሳልማን ባለፈው መስከረም ሴቶች መኪና ማሽከርከር እንዲጀምሩ ፈቃድ ሰጥተዋል።

ባለፈው ወር ደግሞ ሙስናን ለመዋጋት በሚል በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑትንና በአረቡ አለም ሁለተኛ ሀብታም የሆኑት መሐመድ አላሙዲንን ጨምሮ ከ200 በላይ ነጋዴዎች፣ሚኒስትሮችንና የንጉሳዊ ቤተሰብ አባላትን ጠራርገው በቁም እስር ላይ ማዋላቸው ይታወሳል።