(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 23/2009) በሕወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በጎንደር በኩል የሚገኝን አዋሳኝ የኢትዮጵያ ድንበር ለሱዳን ለ10 አመታት በውሰት ለመስጠት በድብቅ መስማማቱን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
ሱዳን ይገባኛል ብላ በተደጋጋሚ የምታነሳው የኢትዮጵያ ድንበር በውሰት ለ10 አመት ከተሰጠ በኋላ ስለመመለሱ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ኮሚሽን ውይይት የቤንሻንጉልና የአማራ ተወካዮች ሲሳተፉ ቢቆዩም ከተደራዳሪነት ውጭ ተደርገው የትግራይ ክልል ሰዎች ብቻ በድንበሩ ጉዳይ ላይ በሚስጥር እየተወያዩ መሆኑም ተነግሯል።
የትግራይ ክልል የመስፋፋት ህልምና የድብቅ ሴራው ማጠንጠኛ የሱዳን በኢትዮጵያ የድንበር ይገባኛል ጥያቄና የቅማንት የማንነት ሕዝበ ውሳኔ መሆናቸውን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
አንዳንዴ በድብቅ ሲያሻቸው ደግሞ በይፋ የሚያሳዩት የትግራይ ክልል አዲሱ ካርታ ከጎንደር ሰፊ መሬት ቆርሶ ከቤንሻንጉል መተላለፊያ ውሽመጥ ሰርቶ ጋምቤላ ድረስ ይዘልቅና የራስ ያለሆነን ማንነት ይመኛል፥ ለወደፊቱ ለመውረስም ያሴራል።
የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት በሱዳን የድንበር ይገባኛል ሰበብ ከጎንደር እየተጠየቁ ያሉ ቦታዎች ሰፊና በርካታ አካባቢዎችን የሚያካትት ነው።
ከነዚህም መካከል ዶሎላ ሶሮቃና አብርሃጅራ በአርማጭሆ በኩል በጭልጋ አውራጃ ደግሞ ሽንፋን ድንበር በማድርግ መተማን፥ ቋራን፥ ቱመትን መንዶካን እና ደላጎን ያተካተቱ መሆናቸውን የድንበሩን ጉዳይ በአንክሮ የሚከታተሉ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
በእነዚህ ከጎንደር ለም መሬቶች እንዲነጠቁ በሕወሃት የተወሰነባቸው አካባቢዎች ኮሪደር 25ና ኮሪደር 26 ተብለው በማእዘናት የተከፈሉ ናቸው።
ከሁለቱም ኮሪደሮች ለሱዳን እንዲሰጥ የተዘጋጀው ሰነድና ካርታ በድብቅ ተይዞ በተወሰኑ ሚስጥረኛ ባለሙያዎች እጅ ይገኛል ተብሏል።
እናም በሕወሐት ሊነጠቁ በሱዳን ድንበር ስም የተከለሉ የጎንደር አካባቢዎች ለ10 አመታት በውሰት ስም ለሱዳን ለመስጠት የኢትዮጵያው አገዛዝ በሚስጥር መስማማቱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ኮሚሽን አማካኝነት የይስሙላ ድርድር እየተካሄደ ቢሆንም ውስጥ ውስጡን ግን የትግራይን ክልል ለብቻው ከሱዳን ድንበር ጋር ለማገናኘት እየተሴረ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በድንበር ኮሚሽኑ ውስጥ የቤንሻንጉል ጉምዝና የአማራ ተወካዮች በኮሚቴው ውስጥ ለስሙ ያሉበት ቢሆንም በሂደት ግን እነሱን በማግለል የትግራይ ክልል ተወካዮች ብቻ ድርድር እያካሄዱ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የሕወሐት ገዥዎች ከቤንሻንጉል ክልል በጉምዝ በኩል ለመውሰድ ካሰቡት የልማት ቦታ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እራሳችንን በክልላችን ውስጥ እናስተዳድር ቢሉም ጉዳዩ በፌደራል የሚወሰን ነው ተብለው እንዲዘገይ ተደርጓል ተብሏል።
ሌላው የትግራይ ክልል ከሌሎች ክልሎች ድንበር ቆርሶ የመስፋፋት ህልም ዋናው ማሳያ ደግሞ በቅማንት ስም የሚካሄደው ሕዝበ ወሳኔ ነው ተብሏል። — ቅማንትን ከአማራ በመነጠል በኋላ ላይ ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ያለመ ሴራና ግብ በማስቀመጥ። ለዚሁም መስከረም 7/2009 በ12 ቀበሌዎች የቅማንት የማንነት ሕዝበ ወሳኔ ለማካሄድ በምርጫ ቦርድ በኩል ታቅዷል።መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቀበሌዎቹን በቅማንት ስር ለማድረግ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ወስነዋል።
በአዲሱ የትግራይ ካርታ ላሊበላ፣ራስ ዳሸን አባይ ግድብና ዋና ዋና ቦታዎችም ተካተው ለሕጻናት ትምህርት ሲሰጥባቸው ከቆዩ በኋላ ሕዥብ ተቃውሞ ሲያሰማ ይቅርታ እንደተጠየቀባቸው መገለጹ ይታወሳል።